ከቤተሰብ አንድ ሰው ግዳጅ ካልገባ እስራትና 20 ሺህ ብር ቅጣት ይጣልበታል - ምርኮኛ ፃድቃን ገብረሚካኤል

81

ህዳር 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) “ከቤተሰብ አንድ ሰው ግዳጅ ካልገባ እስራትና 20 ሺህ ብር ቅጣት ይጣልበታል” ሲል ከአሸባሪው ህወሃት የተማረከችው ፃድቃን ገብረሚካኤል ተናገረች።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ በሚል የማይጨበጥ ተስፋ ሰንቆ በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም ንጹሃንን እየገደለ ሀብት እየዘረፈና እያወደመ ነው።

ይሄንን እኩይ ተግባሩን በቃህ ያሉት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የሽብር ቡድኑን በገባባቸው ቦታዎች ሁሉ እየደመሰሱት ይገኛል።

በሁሉም አቅጣጫ የኢትዮጵያን ህዝብና የፀጥታ ሀይሉን ምት መቋቋም የተሳነው የሽብር ቡድኑ ታጣቂ መፈርጠጥ ጀምሯል፤ ቀሪዎቹ ሙትና ቁስለኛ ሆነዋል።

በመከላከያ ሰራዊቱ ተማርከው ህክምና እየተደረገላቸው ያገኘናቸው የሽብር ቡድኑ የጥፋት ሀይሎች እንዳሉት፤ አሸባሪው የህወሓት ቡድን የትግራይ ወጣቶችን እያስገደደ የጥይት ራት እያደረጋቸው ይገኛል።

የመሰናዶ ትምህርቷን አቋርጣ በሽብር ቡድኑ አስገዳጅነት ወደ ጦር ግንባር የገባችው ተማሪ ፃድቃን ገብረሚካኤል፤ ለሶስት ቀናት መሳሪያ መፍታትና መግጠም ተለማምዳ ነው ወደ እሳት ተማገደችው።

ተማሪ ፃድቃን ለጦርነት ስትገባ ወዳ ሳይሆን ተገዳ መሆኑን "ሁሉም ቤተሰብ የግድ አንድ ሰው ለግዳጅ መላክ አለበት” በሚለው የአሸባሪ ህወሃት ጫና እንደሆነ ገልጻለች።

“ይህ ብቻ አይደለም ልጁን ለግዳጅ ያልሰጠ ቤተሰብ 20 ሺህ ብር ይቀጣል፣ በተጨማሪም እስራት ይጠብቀዋል” ብላለች።

ሌላው ምርኮኛ ወጣት ሀጎስ አረፈአይኔ ለሽብር ቡድኑ እኩይ አላማ ማስፈጸሚያነት የተመለመለበትን አጋጣሚ እንዲህ ይናገራል።

"የእለት ገቢዬን የማገኝበትን የጥልፍ ስራ ለመስራት እየተጓዝኩ እያለ ስብሰባ ብለው ወሰዱን፣ ስንሄድ ስብሰባ አልነበረም፣ በቃ ትዘምታላችሁ ተባልን፣ እኔ አልሄድም ስል ጥይት ተኩሰው አስገድደው አስገቡኝ።" ይላል።

ለምን እንደሚዋጉ ሲጠየቅም "መንግሥት የለም፣ አዲስ አበባ ሂዳችሁ የሽግግር መንግስት  እስከሚመሰረት ጸጥታውን ስትጠብቁ ቆይታችሁ ወደ መቀሌ ትመለሳላችሁ ተብለናል” ሲል ተናግሯል።

የሁለት ቀናት የመሳሪያ መፍታትና መግጠም ስልጠና እንደወሰደ የሚናገረው ምርኮኛው ወጣት አንድ መሳሪያ ለአምስት ተሰጥቷቸው እየተዋጉ እያለ በመከላከያ ሰራዊት በደረሰባቸው ከባድ ምት የሃያ አምስቱን ጓደኞቹን አምስት መሳሪያ ይዞ እጁን ለመከላከያ ሰራዊት መስጠቱን ይናገራል።

በመቀሌ አቅራቢያ ኩኻ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኛ የነበረችው ሌላኛዋ ምርኮኛ ሳምራዊት ጸጋዬ በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት በማቋቋም ትግራይን መገንጠል የትግሉ የመጨረሻ ግብ እንደሆነም ትገልጻለች።

የሸብር ቡድኑ አባላት በገባባቸው ቦታዎች ሁሉ ንብረት ማውደም በሚል መርህ ሀብት እንደሚዘርፍ፣ አብራርታለች።

ትልልቅ ማሽነሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ይጠቅማሉ የተባሉ ንብረቶች ተጭነው መቀሌ እንደሚወሰዱም ገልፃለች።

የሽብር ቡድኑ ለጥፋት የሚያሰማራቸውን ወጣቶች ህዝብን ከህዝብ የሚያቃቅርበትን የተለመደ የከፋፋይ ፕሮፓጋንዳውን ሲያስታጥቃቸው እንደነበር ከሰጡት ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም