ዕድሜ ሳይገድበኝ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን ለመቆም ወደ ግንባር ዘምቻለሁ- ብርጋዴር ጀነራል ካሳዬ ጨመዳ

101

ደብረ ብርሃን  ህዳር 19/2014(ኢዜአ) ሀገርን ለማፍረስ ካሰፈሰፈው የውጭና የውስጥ ጠላቶች ለመከላከል ዕድሜ ሳይገድበኝ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን ለመቆም ወደ ግንባር ዘምቻለሁ ሲሉ ብርጋዴር ጀነራል ካሳዬ ጨመዳ አስታወቁ።
የቀድሞ ጦር መኮንኖች   በሰሜን ሸዋ ዞን  ተገኝተው ወጣቱን እያነቃቁ ይገኛሉ።

ከመኮንኖቹ መካከል ብርጋዴር ጀነራል ካሳዬ ጨመዳ ይገኙበታል።

ብርጋዴር ጀነራሉ ከዚህ ቀደም ሲል "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር አቅንተው እኔ ቤት የምቀመጥበት አንድም ምክንያት የለም፣ ያለኝን የውትድርና ጥበብ ተጠቅሜ ጠላትን ድል ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ማለታቸው ይታወሳል።

ይህንን ወደ ተግባር በመለወጥ ወደ ህልውና ማስከበር ዘመቻው መቀላቀላቸውን ይፋ አድርገዋል።

ሀገርን ለማፍረስ  ካሰፈሰፈው የውጭና የውስጥ ጠላቶች ለመከላከል ዕድሜ  ሳይገድበኝ  ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን ለመቆም ወደ ግንባር ዘምቻለሁ ሲሉ በማረጋገጥ ነው ብርጋዴር ጀነራል ካሳዬ ጨመዳ በሥፍራው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ያስታወቁት።

''ተመልከት ዓላማህን  ተከተል አለቃህን፤  ኢትዮጵያ ወይንም ሞት'' ብለን ከዚህ በፊት ለሃገራችን ዘምተናል ሲሉም ያስታውሳሉ።

አሁንም  የጠቅላይ ሚኒስትሩን  ጥሪ ተከትለን  ዘምተናል ፤ወጣቱ ትውልድ ሊከተለን ይገባል ነው ያሉት።

አሁን ላይ ሃገራችን የገጠማት የህልውና ፈተና ለማለፍ  የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ጠንካራ ክንድ ትሻለች ያሉት ብርጋዴር ጀነራል ካሳዬ፤ ለዚህም ሁሉም ቁርጠኛ ተጋድሎ ማድረግ እንደሚበቅበት ነው ያመለከቱት።

ሌላው  የቀድሞ አየር ወለድ ጦር አዛዥ ወደር የሌለው የኢትዮጵያ የጦር ሜዳሊያ ተሸላሚው  ብርጋዴር ጀነራል ተስፋዬ ኃብተማሪያም በበኩላቸው፤ የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችንን ማሳፈር የዚህ ትውልድ ግዴታ ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያ በቀደሙት ጊዜያት የተነሱባትን ጠላቶች ማሳፈርና ነፃነቷን አስከብራ የቆየችው በጀግኖች አባቶቻችን መስዋትነት ነው ብለዋል።

አሁን ላይ የተነሱባት ጠላቶች ኢትዮጰያን  እየተፈታተኗት መሆኑን ጠቅሰው፤ እነዚህን ጠላቶች በጀግንነት በመፋለም  ነፃነቷን ለማስከበር የወጣቱ ሃይል ተጋድሎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ወጣቱ ትውልድ የመከላከያ ሰራዊቱን በመቀላቀል አሁን የተነሱ ጠላቶችን አሳፍሮ በመመለስ በቀጣይም ማንም የማይደፍራት ኢትዮጵያን መገንባት በጊዜ የለኝም መሳተፍ እንዳለበት ነው  ብርጋዴር ጀነራል ተስፋዬ ያመለከቱት።

ለህልውና ዘመቻው በጦር ግንባር ከመሳተፍ ጎን ለጎን የአካበቢን ሰላም ማስጠበቅና ሰራዊቱን በደጀንነት ማገዝም እንዲሁ።

አሸባሪው ህወሃተ በቀደሙት ዓመታት ህዝብን በመከፋፈል  በሀገር ላይ የረጨው  መርዝ  በማምከን የዜጎችን አንድነትና ሰላም ለማረጋገጥ አሁን ላይ ርብርብ ያስፈልጋል።

ሀገር ከወራሪ ሀይል ለመከላከል የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ግንባር መዝመት የቀደሙ መሪዎችን አኩሪ ታሪክ የደገመ መሆኑን ጠቅሰው፤ እሳቸውም በ80 ዓመታቸው በሚችሉት ሁሉ እያገዙ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም