አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ጎን በመሰለፍ የምዕራባውያንን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ አስተሳሰብ መታገል አለብን-ምሁራን

56

ሀዋሳ ፤ህዳር 19/2014(ኢዜአ).መላው የጥቁር ህዝቦች የፓን አፍሪካኒዝም ዕሳቤ መፍለቂያ ከሆነችው ኢትዮጵያ ጎን በመሰለፍ የምዕራባውያን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ አስተሳሰብን መታገል አለብን ሲሉ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ምሁራን ይናገራሉ።

ምዕራባውያን ኢትዮጵያን በማፍረስ የታሪክ ስብራታቸውን ለመጠገንና አፍሪካን ዳግም በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ለማንበርከክ የተወጠነውን ሴራ  ለመቀልበስ አንድነታችንን ማጠናከር ይኖርብናል።

የዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ጥናት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አወል ዓሊ፤ ምዕራባውያን አፍሪካን  በቅኝ ግዛት በተቀራመቱበት ወቅት ኢትዮጵያን ባለማንበርከካቸው ሲቆጩ እንደነበር አስታውሰዋል።

በተለይ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በኋላቀር የጦር መሣሪያዎችና በባዶ እግር ተዋግተው የአውሮፓ ጀነራሎችን ጭምር በመማረክ ባስመዘገቡት ገድል ውርደት እንደሚሰማቸው ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ላለማስደፈር በቆራጥነትና በአንድነት ባደረጉት ተጋድሎ የተጎናጸፉት ድል ለቀሪው አፍሪካና ለጥቁር ሕዝቦች አሸናፊነት ዓርማ ማስቀመጡን ምሁሩ ተናግረዋል።

በምዕራባዊያን ዘንድ ታሪክ ለማካካስና አፍሪካን አንገት ለማስደፋት ኢትዮጵያን በማፍረስ ስምና ዝናዋን ለማንኳሰስና ታሪኳንም ለማጠልሸት የውስጥና የውጭ ባንዳዎችን ማሰለፋቸውን አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ግንባር ባቀኑበት ወቅት መላው አፍሪካዊያን በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲሰለፉ ያቀረቡትን ጥሪ በመቀበል እየተገኘ ያለው ምላሽ አፍሪካውያን በአንድነት ቆመው ክብራቸውን ማስጠበቅ እንዳለባቸው ያመለክታል ብለዋል።

የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ የወለደው የአፍሪካ ኅብረት ዋና ዓላማው የዳግም ቅኝ ግዛት እሳቤን በተደራጀ መልኩ መመከት መሆኑን ያመለከቱት ምሁሩ፤ በዚህ ረገድ ኅብረቱ የተጣለበትን ኃላፊነት መወጣት እንደሚጠበቅበትም ጠቁመዋል።

አፍሪካን የመበዝበዝ ዓላማቸውን ለማሳካት በተናጠል የሚጥሉትን ማንኛውንም ዓይነት ማዕቀብ ባለመቀበልና በተቀናጀ አግባብ መቀልበስ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን የጀመሩት ምዕራባውያንን የማውገዝ እንቅስቃሴ በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች እንዲደራጁና መብታቸውን እንዲያስከብሩ መነሳሳት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመታቸው የኢትዮጵያን ታላላቅ መሪዎችን እንድናስታውስ ከማድረግም ባለፈ የህልውናው ዘመቻውን ባጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ዶክተር ንጉሥ በላይ በበኩላቸው፤ ምዕራባውያን የታሪክ ስብራታቸውን ለመጠገንና አፍሪካን ለመበዝበዝ ያላቸውን ዕሳቤ ለመተግበር ኢትዮጵያን በተለያዩ ዘዴዎች ለማንበርከክ በመሥራት ላይ ናቸው ይላሉ።

ይህንን እኩይ ዓላማቸውን በግንባር ቀደምትነት ለማራመድ የተሰለፈላቸው ከሃዲውና አሸባሪው የህወሃት ቡድን መሆኑን አመልክተው፤ለዚህም የሐሰት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት ቡድኑን በማጀገን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ይሀም እንቅስቃሴያቸው በተዘዋዋዋሪ መልኩ የጥቁሮች የአሸናፊነት ምልክት የሆነችውን ኢትዮጵያ ማንበርከክን ግባቸው ማድረጋቸው በገሃድ እየታየ መሆኑን ነው ያስረዱት።

እነዚህ አካላት ዘወትር የአፍሪካን የተፈጥሮ ሃብት በመበዝበዝና እርስ በርስ በማጋጨት አድብተው ስለሚሰሩ ከምንጊዜውም በላይ በአንድነት መሰለፍ ይጠበቅብናል ነው ያሉት ዶክተር ንጉሥ።

በተለይ የፓን አፍሪካኒዝም ዕሳቤ መፍለቂያ የሆነችው ኢትዮጵያ አሁንም እየተጣራች ነው ያሉት ምሁሩ፤ አፍሪካውያንና ሌላውም መላው ጥቁር ሕዝቦች በመደራጀት የምዕራባውያኑ ያልተገባ እንቅስቃሴና ሴራ  ማክሸፍ አንዳለባቸው አመልክተዋል።

የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ  አህመድ በቅርቡ፤  ለጥቁር ሕዝብ ክብርና ልዕልና ስትሉ በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ሁላችሁም ጥቁር ሕዝቦች ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቆሙ ጥሪ አቀርብላችኋለሁ ሲሉ መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም