ነዋሪዎቹ 115 ሠንጋ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ለገሱ

83

ጅማ፤ ህዳር 19/2014(ኢዜአ). በጅማ ዞን የኦሞ ናዳ ወረዳና ሰኮሩ ወረዳ ነዋሪዎች 115 ሠንጋ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ለገሱ።
በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎችም ለሀገር ህልውና የህይወት ዋጋ እየከፈለ ላለው ለጀግናው መከላከያ ሠራዊት የተለያዩ ድጋፎች እየሰበሰቡ ነው።

ከእነዚህም የኦሞ ናዳ ወረዳ ነዋሪዎች 93 ሰንጋ የሰኮሩ ወረዳ ደግሞ 22 ሠንጋዎች መለገሳቸውን የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር ናቸው የገለጹት።

ለሀገር ክብርና ሉአላዊነት መጠበቅ ህይወት ለሚከፍለው የመከላከያ ሃይላችን እስከመጨረሻው ድል  ከጎኑ በመሰለፍ ልናግዘው  ይገባልም ብለዋል።

በኦሞ ናዳ ወረዳ ድጋፉ በተደረገበት ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል  የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ  አቶ አብዱረህማን አብደላ እንደገለጹት፤ህዝቡ  ለመከላከያ ሠራዊት እየተደረገ ያለው የደጀንነት ድጋፍ  አበረታች ነው።

ህዝቡ በግንባርም ሆነ በደጀንነትም የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።

ከዞኑ ከሁሉም ወረዳዎች  የሚሰባሰበው የተዘጋጀ ስንቅ፣ የገንዘብና  የሠንጋ በሬዎች ድጋፍ  ስራ መቀጠሉም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም