በአሚሶም ጥላ ሥር የተሰማራው የኢትዮጵያ ሠራዊት ግዳጁን በተሳካ ሁኔታ እየፈጸመ ነው

67
ሶማሊያ ነሃሴ 16/2010 በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ሠራዊት (አሚሶም) ጥላ ሥር የተሰማራው አራተኛው ዙር የኢትዮጵያ ሠራዊት ግዳጁን በተሳካ ሁኔታ እየፈጸመ መሆኑን አስታወቀ። በአሚሶም የቀጣና ሦስት ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል አሰፋ ቸኮል እንዳሉት፤ ሠራዊቱ የሶማሊያ ህዝብና መንግሥትን ለመደገፍ የተጣለበትን ተልዕኮ በመወጣት ላይ ይገኛል። ለሶማሊያ ፖሊስ፣ ሚሊሺያ፣ ለክልልና ለመደበኛ ሠራዊት ተከታታይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንደተሰጠ ገልጸው አልሻባብን ለመደምሰስ በርካታ የኦፕሬሽን ሥራዎች መሥራታቸውን ጠቁመዋል። ከሶማሊያ ሠራዊት ጋር በመተባበር በተካሄዱ የኦፕሬሽን ሥራዎች በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ ጉዳት አለመድረሱን የጠቀሱት ዋና አዛዡ ''ሠራዊቱ ግዳጁን በተሳካ ሁኔታ እየተወጣ መሆኑን ያሳያል'' ብለዋል። ሠራዊቱ የአልሻባብን የውጊያ ስልት በማጤኑ በሽብር ቡድኑ የሰው ህይወትና ንብረት ላይ የሚያደርሰውን አደጋ መመከት እንደቻለም ገልጸዋል። በተጠናቀቀው ዓመት በመሬት ላይ የተቀበሩ 56 ፈንጂዎችን ማምከን እንደተቻለ የገለጹት ብርጋዴር ጄነራል አሰፋ ሠራዊቱ የሽብር ቡድኑን ከመደምሰስ ጎን ለጎን በበርካታ የልማት ሥራዎች ላይ በመሰማራት የሶማሊያ ሕዝብና መንግሥትን ሲደግፍ መቆየቱን ተናግረዋል። በተለይ የውኃ መስመር ዝርጋታዎችና በአልሸባብ የተዘጉ መንገዶችን ማስከፈት በሠራዊቱ የተከናወኑ ተግባራት ሲሆኑ ከመደበኛ ቀለብ ላይ ተቀናሽ በማድረግ ለተፈናቃዮች የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አብራርተዋል። “በአሁኑ ወቅት ባይደዋ ሰላም የሰፈነባት ከተማ በመሆኗ የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮች የሚመላለሱባት ሆናለች“ ያሉት ብርጋዴር ጄነራል አሰፋ ሠራዊቱ ከአከባቢው ማኅበረሰብ፣ ከጎሳ መሪዎች፣ ከሴትና ከወጣት አደረጃጀቶች እንዲሁም ከአስተዳደርና ከፀጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። ''በአሚሶም ጥላ ሥር የተሰማራው አራተኛው ዙር የኢትዮጵያ ሠራዊት በአንድ ዓመት ውስጥ በሶማሊያ ከሚያስተዳድረው ቀጣና 350 የአልሸባብ አባላትን መደምሰስና መማረክ ችሏል'' ሲል በስፍራው የሚገኘው የኢዜአ ሪፖርተር ዘግቧል። በሶማሊያ ስድስት የአፍሪካ አገሮች የተሳተፉበት የሰላም አስከባሪ ሠራዊት በስድስት ቀጣናዎች ተዋቅሮ ግዳጁን እየተወጣ ሲሆን ቀጣና ሦስት በኢትዮጵያ ሠራዊት ሙሉ በሙሉ ሲተዳደር ሁለት ቀጣናዎች ደግሞ በከፊል በስሩ ይተዳደራሉ። አሚሶም በሶማሊያ የሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች ከአገሪቱ የቆዳ ስፋት 74 በመቶውን ሲሸፍን ከአራት ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ሠራዊት በስፍራው የሚገኝ ሲሆን የሠራዊቱ ብዛት ከኡጋንዳ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም