ከውጭ ጠባቂነት ለመላቀቅ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ አማራጮችን ለመጠቀም መረባረብ ይገባል

68

አርባ ምንጭ ፤ ህዳር 18/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ከውጭ ጠባቂነት ለመላቀቅ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ አማራጮችን ለመጠቀም መረባረብ እንደሚገባ የግብርና ሚኒስቴር አመለከተ።

ሀገር አቀፍ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ይፋዊ የዘር ማስጀመሪያ መርሀ ግብር በጋሞ ዞን በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ዛሬ ተካሂዷል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለሰ መኮንን በወቅቱ እንደተናገሩት ፤መንግሥት በምግብ ሰብል ራስን በመቻል ከውጭ ጠባቂነት ለመላቀቅ ለስንዴ ልማት ትኩረት ሰጥቷል።

አርሶ አደሩና በግብርና ልማት የሚሳተፉ አካላት ለልማቱ ትኩረት በመስጠት ሥራውን እንዲያካሂዱም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ከምዕራባውያን ጠባቂነት ለመውጣት እየሰራች ባለችበት ወቅት ከአሸባሪው ህወሃት ጋር በመሆን በማዳከም አፍሪካን ለመቆጣጠር እየተሯሯጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ህወሀት በምዕራባውያን ጋላቢነት የደቀነብንን የህልውና አደጋ ለመመከት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀሩ በግንባር መሰለፋቸውን ጠቁመው፤አመራሩ ከሕዝቡ ጋር በመሆን ወደ ልማት መግባቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ሁሉንም ዓይነት ሰብል፣ አትክልት፣ ፍራፍሬና የእንስሳት ባለቤት መሆኗን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ አርሶ አደሩ በመስኖ፣ በበልግና በመኸር ስንዴና ሌሎች ሰብሎች ላይ አተኮሮ እንዲያለማ መረባረብ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ከተጋረጠባት አደጋ ለመውጣት ከአሸባሪዎችና ከድህነት ጋር ጦርነት ገጥማለች ብለዋል።

በሁለቱም ጦርነቶች አሸናፊ ለመሆን በመደመር እሳቤ በቁጭትና በአንድነት ተነስተን በትጋት መስራት ይገባናል ነው ያሉት።

የምግብ ዋስትናዋን ያላረጋገጠች ሀገር ሉዓላዊነቷ ችግር ውስጥ ይወድቃል ያሉት አቶ ኡስማን፣ የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችና ግብአቶችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት መተካት አለብን ብለዋል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራ የሕዝቡን የኢኮኖሚ ደረጃ በመሠረታዊነት እንደሚቀይር ጠቁመው፣ከምግብ ዋስትናው በተጨማሪ ለበርካታ ዜጎች በተለይም ለሴቶችና ወጣቶች ሥራ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

''ውሃ፣ መሬት፣ ጉልበት እያለን ባለመስራታችን ህዝባችንን አስርበናል ሀገራችንንም ለልመና ዳርጎናል'' ያሉት ሃላፊው፤ ዘንድሮ የመስኖ ልማቱን በቁጭትና በተግባር ለመካስ ሁሉም ለስኬታማነቱ እንዲተጋ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ፤ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን በአግባቡ ማልማትና ጥቅም ላይ ማዋል ባለመቻላችን በጎርፍና ናዳ ምክንያት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል ብለዋል፡፡

ለመስኖ ልማት መዋል የሚችሉ የተፈጥሮ ፀጋዎችን ወደ ልማት በማዞር በርትተን በመስራት የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ይጠበቅብናል ብለዋል።

በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ቆላሻራ ቀበሌ አርሶ አደር ይርጋለም መንገሻ ፤በመርሐ በመስኖ ስንዴ ለማምረት ሦስት ሄክታር ለማልማት እንደተዘጋጁ ተናግረዋል።

በማሳቸው ለሚያለሙት ስንዴ ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ እንዳገኙ የገለጹት አርሶ አደሩ፣ዘንድሮ የሚያገኙትን ምርት በማየት በቀጣይ በስፋት እንደሚያለሙም ገልጸዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ በ2014 የምርት ዘመን ከ400 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ስንዴ በበጋ መስኖ በማልማት 16 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እንደታቀደ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም