አሸባሪ ቡድኑን በአንድነት ሆነን የምናጠፋበት እንጂ ተደላድለን የምንቀመጥበት ጊዜ ላይ አይደለንም

81

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሀገር ሊያፈርስ የመጣውን አሸባሪ ቡድን በአንድነት ሆነን የምናጠፋበት እንጂ ተደላድለን የምንቀመጥበት ጊዜ ላይ አይደለንም ሲሉ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሀገር ላይ የህልውና አደጋ ከደቀነበት ጊዜ አንሰቶ ሁሉም ህዝብ የአገሩን አንድነት ለማስጠበቅና እነዚህን የአገር ከሃዲዎች ለማጥፋት እየተረባረበ ይገኛል።

በዚህም ለአገር መከላያ ሰራዊት የተለያዩ ድጋፎችን ከማድረግ እስከ መዝመት የደረሱ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው።

ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው የመጣን ማንኛውንም ሀይል እንደማይታገሱና አስፈላጊውን መስዋእትነት ሁሉ ከፍለው ሀገራቸውን እንደሚያስቀጥሉም በተግባር እያስመሰከሩ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም በጦር ግንባር ሆነው ሰራዊቱን በመምራት ላይ ይገኛሉ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ  የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቆራጥ ውሳኔ አድንቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን ለማዳን ግንባር ድረስ መዝመትና ጦርነቱን መምራት ለአገራቸው ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር የሚያሳይ መሆኑን በመግለጽ ይህም ለሰራዊቱም ሆነ ለህዝቡ ትልቅ ሞራል ነው ብለዋል።

በተለይ ወጣቶች አገራቸውን ከአሸባሪው ነጻ ለማድረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው እንደ አባቶቻችን የህዝባችንን ነጻነት ማስቀጠል አለባቸው ብለዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ  ባለው አቅም በገንዘብ፣ በጉልበትና በመዝመትም ጭምር የአሸባው ህወሓትን ግበዓተ መሬት በአንድነት ሆኖ ማፋጠን እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።

ህዝቡ አሁን ያለንበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን አውቆ አካባቢውን በንቃት በመቃኘት አጠራጣሪ ነገር ሲኖር በፍጥነት ለጸጥታ አካላት መጠቆም አለበት ብለዋል።

አሻበሪው ቡደን በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የኢትዮጵያን ህዝብ በሃይማኖት፣ በብሔር በመከፋፈል የአገሪቱን አንድነት አደጋ ውስጥ ከቶ እንደነበር ጠቁመዋል።

አሸባሪውን ቡድን እራሱ ባዘጋጀው ጉድጓድ ውስጥ በመቅበር የአገራችንን ነጻነት ማረጋገጥ አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም