ከጌዴኦ ዞን ከቡና ሽያጭ 127 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት እየተሰራ ነው

133

ዲላ፣ ኅዳር 18/2014 (ኢዜአ) ከጌዴኦ ዞን ለማዕከላዊ ገበያ ከሚቀርበው ቡና 127 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ የልማቱ ተሳታፊዎች ጦርነቱ በውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማቅረብ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ እንዳስታወቀው በጀት ዓመቱ 29 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ  127 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት እየተሰራ ነው።

በተያዘው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን ቡና ካለፈው በጀት ዓመት በ7ሺህ ቶን ለመጨመር መታቀዱን መምሪያው አስታውቋል።

በዞኑ ይርጋጨፌ ወረዳ የቆንጋ ቀበሌ አርሶ አደር ሽብሩ ሹፎ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ በሶስት ሄክታር ማሳቸው ላይ ልዩ ጣዕም ቡና  በማምረትና በማዘጋጀት በቀጥታ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል።

ዘንድሮም ተጠቃሚነታቸውን ለማስቀጠልና ጦርነቱ  በውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ልዩ ጣዕም ቡና በብዛት ወደ ውጭ ለመላክ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ባለፈው አመት ለውጭ ገበያ የላኩትን 3 ሺህ 500 ኪሎ ግራም  ልዩ ጣዕም ቡና ዘንድሮ ወደ  6 ሺህ ኪሎ ግራም በማሳደግ ለውጭ ምንዛሪው ግኝት እንዲያድግ በመሥራት ላይ እንደሚገኙ አቶ ሽብሩ ተናግረዋል።

መንግሥት ባመቻቸላቸው ስልጠና በመታገዝ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ሺህ ኪሎ ግራም  የቡና ዘር በማዘጋጀት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በገጠማት የውስጥና የውጭ ሃይሎች የተቀናጀ ጫና ቁጭት ተሰምቶኛል ያሉት አርሶ አደሩ፣ይህንን ለመቀልበስ እየተካሄደ ላለው የህልውና ዘመቻ ስኬታማነት ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"አገራችንን በምንችለው ሁሉ በመደገፍ የተደቀነብንን የህልውና አደጋ ከመቀልበስ በተጓዳኝ የልማት ሥራዎች እንዳይስተጓጎሉ  በተሰማራንበት የሥራ መስክ ጠንክረን ልንሰራ ያስፈልጋል" ያሉት ደግሞ የወረዳው አርሶ አደር አብርሃም አገዘ ናቸው።

ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስር ከ11 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ልዩ ጣዕም ቡና በየዓመቱ አዘጋጅተው ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንደሆኑ ገልጸዋል።

'በአርሶ አደሩ ልፋት የራሱን ኪስ የሚያደልበው የህወሓት ቡድን ዳግም እንዳይመጣ ለመከላከያ ሠራዊት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ በተያዘው ዓመት የተሻለ ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ለውጭ ምንዛሪ ግኝቱ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ለማሳረፍ እንደሚሰሩ አቶ አብርሃም አስታውቀዋል።

ከምርት አሰባሰብ እስከ ዝግጅት ድረስ ከ72 ለሚልቁ ዜጎች ሥራ መፍጠራቸውን አስታውቀዋል።

በወናጎ ወረዳ የቱማታ ቀበሌ የእሸት ቡና ኢንዲስትሪ ባለቤትና ቡና አቅራቢ አቶ ኡመር አብዱ በዚህ ዓመት  አንድ ሺህ ኩንታል የታጠበ ቡና ለገበያ ለማቅረብ እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በተለይ በውጭ ገበያ ሊፈጠር የሚችለውን ጫና ለመቋቋምና ተወዳዳሪ ለመሆን ጥራትን መሰረት አድርገው በመሥራት ላይ እንደሚገኙና በእንቅስቃሴያቸውም ለ350 ዜጎች ሥራ መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

በምርት አሰባሰብ ሂደት ምንም አይነት ብክነት እንዳይኖርና ሕገ ወጥ የቡና ዝውውርን ለመቆጣጠር ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ሃላፊ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ ናቸው።

በዞኑ 207 የግል የእሸት ቡና ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ ማህበራት፣ ዩኒየኖችና ከ500 የሚልቁ የልዩ ጣዕም ቡና አምራች አርሶ አደሮች ቡናን በጥራት እያዘጋጁ ለገበያ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህ እንቅስቃሴ ዘንድሮ ከ29 ሺህ ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለማቃለል ጭምር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በበጀት አመቱ ከዞኑ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ከታቀደው የቡና ምርት 127 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን አብራርተዋል።

በጌዴኦ ዞን ከ70 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ተክል የተሸፈነ ሲሆን፣ በልማቱም ከ120 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች  መሰማራታቸውን ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም