ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን በጋራ እንታደግ በማለት ላቀረቡት ጥሪ ወደ ኋላ የምንልበት አንዳች ምክንያት የለም

62

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን በጋራ እንታደግ በማለት ላቀረቡት ጥሪ ወደ ኋላ የምንልበት አንዳች ምክንያት የለም" ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው አንጋፋ ድምጻዊያን ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያውያን  በግንባር ከመሰለፍ ባሻገር በሙያቸውና በገንዘባቸው ድጋፍ በማድረግ ለአገራቸው ህልውና መጠበቅ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን በጋራ እንታደግ በማለት ላቀረቡት ጥሪ ወደ ኋላ የምንልበት አንዳች ምክንያት የለም ሲል ለኢዜአ የገለጸው ድምጻዊ ጸጋዬ እሸቱ ነው።

የትኛውንም ጉዳይ ማከናወን የሚቻለው በቅድሚያ አገር ሲኖር መሆኑን ጠቅሶ፤ ከዚህ አኳያ ለኢትዮጵያ ህልውና መሰዋዕት ለመሆን ጭምር ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

ድምጻዊ ግርማ ተፈራ በበኩሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የጸጥታ ኃይሎች ለአገራቸው ሉዓላዊነት እየከፈሉት ያለውን መስዋዕትነት አድንቋል፡፡

በሙያው ሰራዊቱን ሲያነቃቃ መቆየቱንም ነው ያነሳው፡፡

"የትም ዞሬ መግቢያዬ አገሬ ኢትዮጵያ ናት፤ ሌላ አገር የለኝም" ያለው ድምዓዊ ግርማ ተፈራ፤ ለህልውና ዘመቻው ስኬት የሚጠበቅበትን ሁሉ አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ድምጻዊ አቦነሽ አድነው በተለያዩ ቋንቋዎች ባበረከተቻቸው ሙዚቃ ስራዎች የአገሯን ባህል ለዓለም አስተዋውቃለች፡፡

በተለይ "ባህሌን" በሚለው ስራዋ የኢትዮጵያውያን ባህል እሴትና አኗኗር በዘፈን ክሽን አድርጋ አሳይታለች፡፡

ድማጻዊ አቦነኝ አድነው ከዘጠኝ ዓመት በፊት ዓለማዊ ዘፈን በማቆም ወደ መንፈሳዊ ዝማሬ መግባቷ ይታወቃል፡፡

"ዘፈን ካቆምኩ ዘጠኝ ዓመት ቢሆነኝም ዳግም በሙያዬ ማገልገልን ጨምሮ ለህልውና ዘመቻው የሚጠበቅብኝን ሁሉ ለማበርከት ዝግጁ ነኝ" በማለት ነው የተናገረችው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም