የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ላይ የተጋረጡትን ችግሮች ለመቋቋም በዲፕሎማሲው መስክ ጥረቶች እየተደረጉ ነው

115

ህዳር 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ላይ የተጋረጡትን ችግሮች ለመቋቋም በዲፕሎማቶች በኩል የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ፡፡

በመላው ዓለም ያሉ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችና የዋናው መስሪያ ቤት ስራ ሃላፊዎች ዓመታዊ ስብሰባ እየተካሄደ ነው፡፡

ስብሳበውን አስመልክተው ለኢዜአ ማብራሪያ የሰጡት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዓመታዊ ስብሰባው ባለፈው በጀት ዓመት የነበረው አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እየተካሄደበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያን ጥቅም በውጪው ዓለም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በሌሎችም ዘርፎች ለማስጠበቅ የተደረጉ ጥረቶችና ባጋጠሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ ውይይት መካሄዱን ገልጸዋል፡፡

በተለይም ህዳሴ ግድብን ከግብ ማድረስ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ በርካታ ጥረቶች ሲካሄዱ ቆይተው በዚህም የተለያዩ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚሁ ውይይት እየተካሄደ ባለው የህልውና ዘመቻና ከዚህ ጋርም ተያይዞ ከአንዳንድ አገራት እየተስተዋለ የሚገኘውን ጫና ለመቋቋም በዲፕሎማሲው መስክ መሰራት ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያም ውይይት መካሄዱን አስረድተዋል፡፡

ከኢትዮ-ሱዳን የድንበር አካባቢ የተፈጠረው ውዝግብን ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች ምን ይመስሉ እንደነበርም በውይይቱ መነሳቱን ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያ የውጪ ግንኙነት እንቅስቃሴዎች ጉዳይ ዙሪያም በዓመታዊ ስብሰባው ላይ እየተመከረ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡     

“በኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ላይ የተጋረጡትን ችግሮች ለመቋቋም በተደረጉ ጥረቶች ከአንዳንድ አካላት ኢትዮጵያ ላይ የሚያደረጉትን ጫና ለመቋቋም ዲፕሎማቶች ከኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና ከኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር በመተባባር ያደረጓቸው እንቅስቃሴዎች እንደ አንድ ውጤት ተነስቶ ውይይት ተካሂዶበታል” ብለዋል፡፡

በዚህም ጫናዎቹ እንዳሉ ሆነው በአንዳንዶች አካባቢዎች የመርገብ ሁኔታዎች እና ውጤቶችም መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

ለምሳሌም በሰሜን አሜሪካ በቨርጂኒያ ኢትዮጵያኖች ባደረጉት እንቅስቃሴ የተገኙ ውጤቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያውያኖች እና ትውልደ ኢትጵያውያኖች ከአሜሪካ ሴናተሮች፣ ከኮንግረስ አባላት፣ በአካባቢው ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ ከተለያዩ ወገኖች ጋር እየተገናኙ የኢትዮጵያን አቋም ማስረዳታቸውንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ አቋም ምን እንደሆነ በመግለጽ ረገድ ያደረጓቸው እንቅስቃሴዎች ጎልተው መታየታቸው እንደ ውጤት መወሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በመላው ዓለም ያሉ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች እና የዋናው መስሪያ ቤት ስራ ሃላፊዎች ዓመታዊ ሰብሰባ ከህዳር 15 እስከ 18 የሚካሄድ መሆኑም ታውቋል፡፡

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም