በመላው ዓለም የሚገኙ ዳያስፖራዎች በቋሚነት ድጋፍ የሚያደርጉበት የባንክ ሂሳብ ቁጥር እንዲከፈት እንቅስቃሴ ተጀምሯል

60

አዲስ አበባ ህዳር  17/2014 (ኢዜአ) በመላው ዓለም የሚገኙ ዳያስፖራዎች በቋሚነት ለኢትዮጵያ ድጋፍ የሚያደርጉበት የባንክ ሂሳብ ቁጥር እንዲከፈት እንቅስቃሴ መጀመሩን ኢዜአ ያነጋገራቸው በአሜሪካ የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ገለጹ።

በመላው ዓለም በውጭ አገራት የሚኖሩ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙ ይገመታል።

በውጭ አገር የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ለወቅታዊ አገራዊ ጥሪዎችና ለልማት ፕሮጀክቶች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑ ይታወቃል።

በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዳያስፖራው ለአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለሰብዓዊ ድጋፎችና ለዜጎች መልሶ ማቋቋም ከ125 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት አድርጓል።

በተመሳሳይ በሩብ ዓመቱ ለአገራዊ ፕሮጀክቶች ከ251 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት ከዳያስፖራው መሰብሰቡን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ ድጋፍ ከሚያደርግባቸው መንገዶች አንዱ ለወቅታዊ ሁኔታዎች በተለያዩ  ዘርፎች የሚከፈቱ የተለያዩ የባንክ ሂሳብ ቁጥሮች ነው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው በአሜሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በውጭ አገራት የሚኖሩ ዜጎች በተለያዩ የሂሳብ ቁጥሮች ገንዘባቸውን መላካቸው አገራቸውን ለመርዳት ያላቸውን ፍላጎት የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ በተለያየ የሂሳብ ቁጥር ገንዘብ መላኩ የዳያስፖራውን ድጋፍ በአንድ ማዕቀፍ ውስጥ ያልተሰበሰበና አገር በዘላቂነት ለመደገፍ የሚያስችል አይደለም ብለዋል።

ስለዚህም በመላው ዓለም የዳያስፖራው ማህበረሰብ አባላት በቋሚነት ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ መላክ ያለውን ዘለቄታዊ ጥቅም አስመልክቶ ጥናት በማድረግ ረቂቅ ሰነድ ማዘጋጀታቸውን ዳያስፖራዎቹ ገልጸዋል።

በተደረገው ጥናት በአሜሪካ 250 ሺህ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በቋሚነት ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ መታወቁንና የሂሳብ ቁጥር መንግስት እንዲከፍት የሚጠይቀውን እንቅስቃሴ የሚያስተባብር ኮሚቴ መዋቀሩን ጠቁመዋል።

የሂሳብ ቁጥሩ መዘጋጀቱ ዳያስፖራው በአንድ ቋት ገንዘብ ወደ አገሩ በመላክ ኢትዮጵያን በዘላቂነት መደገፍ ይቻላል ብለዋል።

በቋሚነት የሚላከው ገንዘብ መንግስት በአጭር ጊዜ ጦርነቱ ካለቀ በኋላ ለመልሶ ማቋቋም፣ በመካከለኛ ጊዜ ለልማት ፕሮጀክቶችና በረጅም ጊዜ ለማህበራዊ አገልግሎቶች ማስፋፊያ መጠቀም እንደሚቻል አመልክተዋል።

በመላው ዓለም የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ለመክፈት በሚታሰበው ቋሚ የሂሳብ ቁጥር ገንዘባቸውን ከላኩ ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት ድህነት ማውጣት ይቻላል ነው ያሉት ዳያስፖራዎቹ።

መንግስት በዳያስፖራው አማካኝነት በሚያገኘው ቋሚ ድጋፍ ከእርዳታና ብድር መላቀቅ እንደሚችልም ተናግረዋል።

ወጥነት ባለው መልኩ ዳያስፖራው የሚያደርገው ድጋፍ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም ዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ ገንዘቡን ወደ አገር ቤት እንዲልክ የሚያነሳሳና የሚያበረታታ እንደሆነም ነው ዳያስፖራዎቹ የገለጹት።

የቺካጎ ከተማ ነዋሪው አምባሳደር በፍቃዱ ረታ እንዳሉት የተፈናቀሉ ወገኖችን   ለማቋቋሚያ ና ፕሮጀክቶችን ለማፈጸም ሬሚታንስ ከዳያስፖራው እንደሚያሰባሰቡ ተናግረዋል።

ዳያስፖራ ወገቡን አስሮ አገሩን መርዳት ቢጀምር አገር ካላችበት ማቅ ውስጥ ያወጣታል  የሚሉት ደግሞ አቶ አቢይ ገብረሕይወት በዋሺንግተን ዲሲ ነዋሪ።

በመላው ዓለም የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በቋሚነት ለኢትዮጵያ ድጋፍ የሚያደርጉበትን የአሰራር ስርዓት ለማበጀት እየተደረገ ያለውን ጥረት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስት ከባንኮች ጋር በመሆን ዳያስፖራው የውጭ ምንዛሬን ቀላል በሆነ መልኩ የሚልኩበት የቴክኖሎጂና የአሰራር ስርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ባለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት በአማካይ 3 ቢሊዮን ዶላር (ሬሚታንስ) መላኩን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዳያስፖራው ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ መላኩን ኤጀንሲው ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም