የጠቅላይ ሚኒስትሩ መዝመት ለሀገራችን ክብር እንድንቆም አነሳስቶናል- ወጣቶች

81

ነቀምቴ ህዳር 17/2014 /ኢዜአ/ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ጦር ግንባር መዝመት ለሀገራችን ክብር እንድንቆም አነሳስቶናል ሲሉ - የነቀምቴ ከተማ ወጣቶች አስታወቁ።
የከተማው ወጣቶች ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

የአከባቢያቸውን ሠላም ከመጠበቅ ጀምሮ የአገር መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል የአገር ሉዓላዊነት ለማስከበር መዘጋጀታቸውን ወጣቶቹ ለኢዜአ አስታውቀዋል።

ከወጣቶቹ መካከል የቀሶ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ቀኖ ገረመው በሰጠው አስተያየት " የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጦር ግንባር መዝመት ለሀገራቸው ሉአላዊነት መከበር ያላቸውን ጽናት አሳይቶናል።

"የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ወጣቶች ያለንበት ወቅት የአገርን ሉዓላዊነትን ለማስከበር ከጎናቸው በመቆም አለኝታነታችንን በተግባር የምናረጋግጥበት ወቅት መሆኑን እንድንገነዘብ አድርጎናል " ብሏል፡፡

"እኛ እያለን ኢትዮጵያ አትፈርስም" ያለው ወጣት ቀኖ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ፈለግ በመከተል የሀገርን ህልውና ለማስከበር እስከ የህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል መወሰኑን አስታውቋል።

ሌላው የክፍለ ከተማው ነዋሪ ወጣት ሮማን አብደታ በበኩሏ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጦር ግንባር መዝመት ከፍተኛ ተነሳሽነት የፈጠረላት በመሆኑን ተናግራለች።

"ከጎናቸው በመቆም አገርን ከማፈራረስ አደጋ ለማዳን የአገር መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል ወስኛለሁ" ስትል አቋማን ገልጻለች፡፡

የበከ ጀማ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ፈቀደ ፍቃዱ በበኩሉ የአገርን ነፃነት ለማስከበር የአገር መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል የህወሓትን አገር የማፈራረስ ከንቱ ምኞት ለማክሸፍ ቁርጠኛ መሆኑን አመልክቷል፡፡

አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የያዘውን ዓላማ ለማክሸፍ የአካባቢውን ሠላም ከመጠበቅ ጀምሮ የአገር መከላከያ ሠራዊትን እስከ በመቀላቀል ዝግጁ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የደርጌ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት አቦማ መኮንን ነው፡፡

የከተማው የወጣቶች ሊግ ኃላፊ አቶ ገላና ታመነ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት በህዝቦች የሕይወት መስዋዕትነት በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስና አገርን ለማፈራረስ የሚያደርገውን ከንቱ ምኞት ለማክሸፍ ወጣቱ በቁርጠኝነት መነሳሳቱን ገልፀዋል።

የከተማው ወጣቶች የአገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር አከባቢያቸውን ለመጠበቅና ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን ለመቆም መዘጋጀታቸውን በማረጋገጥ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል ።

በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትሩን መዝመትና ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ ወጣቱ በከፍተኛ ወኔ ከጎናቸው ለመቆም እየተነሳሳ መሆኑን አመልክተዋል ።

በብልጽግና ፓርቲ የነቀምቴ ጽህፈት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስፋው ታዬ የከተማው ወጣቶች አገር መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል፣ ድጋፍ በማሰባሰብና የአካባቢያቸውን ሠላም በማረጋገጥ የማይፋቅ ታሪክ ለመስራት ራሳቸውን ማዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ወጣቶቹ ውይይታቸውን ሲያጠናቅቁ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ደም ለግሰዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም