በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ዓለም አቀፍ የሚዲያ ዘመቻ ለመመከት የአገር ውስጥ ሚዲያዎች የተቀናጀ ስራ ይጠበቅባቸዋል

59

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ እያካሄዱት ያለውን የተቀናጀ ዘመቻ ለመመከት በተለይም የአገር ውስጥ ሚዲያዎች የተቀናጀና የተጠናከረ ስራ ይጠበቅባቸዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እንደተናገሩት፤ አሜሪካና የምዕራቡ ዓለም አገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ሊያስጠብቅላቸው ከሚችለው ሁኔታ ጋር ራሳቸውን ማጣመር ላይ ተጠምደው እየሰሩ ነው።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና እያሳደሩ መሆኑን ገልጸው፤ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ እያካሄዱት ያለውን የተቀናጀ ዘመቻ በመመከት እውነታውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስረዳት የአገር ውስጥ ሚዲያዎች የተቀናጀና የተጠናከረ ስራ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

አሜሪካና የምእራቡ ዓለም አገራት ዓላማ ኢትዮጵያን ማዳከምና የተበታተነች አገር በማድረግ መንግስትን እነርሱ በሚፈልጉት መልኩ ፈጥረው ታዛዥ ለማድረግ በማሰብ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል።

የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ከፍተኛ አማካሪ እና የዋርካ መልቲሚዲያ ኩባንያ ዋና ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ እሸቱ ገለቱ፤ ምዕራቡ ዓለም ከኢትዮጵያ በተቃራኒ የቆመበት የተለያየ ምክንያት ቢኖራቸውም ዋነኛው የራሳቸውን ጥቅም ማስከበር ላይ እንደሆነ አስገንዝቧል።

የዋልታ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ስንታየሁ አባተ በበኩሉ የምዕራባውያን አገራት መገናኛ ብዙሃን ከኢትዮጵያ በተቃራኒ የቆሙት እውነታው ጠፍቷቸው ሳይሆን የምዕራባውያኑ የበላይነትን ይዞ የመቆየት ፍላጎት እንደሆነ ተናግሯል።

የድሬ ቲዩብ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ፍሬው አበበ "በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአገራችን ላይ ተጽእኖ በማሳደር የተቀናጀ ጥቃት ለማድረስ ያለመ ነው" ሲል የምዕራባውያኑን የተቀናጀ ዘመቻ ገልጾታል።

የኢትዮጵያ መንግስትን እነሱ በሚፈልጉት መልኩ እጁን ጠምዝዘው ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ እየሰሩ እንደሆነም አመላክቷል።

አገር እንዲህ አይነት ፈታኝ ወቅት ላይ በምትሆንበት ጊዜ በተለይ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የሚሰሯቸው ዘገባዎች የተጠኑና በቂ ዝግጅት የተደረገባቸው ሊሆኑ እንደሚገባ ባለሙያዎቹ መክረዋል።

"የሚዲያዎቹ ዜና እና ፕሮግራም ይዘቶች አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ እንዲሆኑ በመስራት የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማድረስ ይገባል" ብለዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣ _

ወደ ግንባር ዝመት፣_

መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም