ሉሲዎቹ ለሴካፋ ውድድር የሚያደርጉት የሩዋንዳ ጉዞ ተሰረዘ

80
አዲስ አበባ ግንቦት 9/2010 የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለሶስተኛ ጊዜ በሚካሄደው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገራት የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ዛሬ ወደ ሩዋንዳ ሊያደርግ የነበረው ጉዞ መሰረዙን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) እስካሁን ስለ ውድድሩ መካሄድ የሰጠው ማረጋገጫ ባለመኖሩ የሉሲዎች የዛሬ የሩዋንዳ ጉዞ መሰረዙን ገልጿል። ፌዴሬሽኑ ስለ ውድድሩ መካሄድ አለመካሄድ ከሴካፋ ምላሽን እየጠበቀ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። በአሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን  ለውድድሩ እንዲረዳው ላለፉት ሁለት ሳምንታት 23 ተጫዋቾችን ይዞ በአዲስ አበባ ስታዲየም ልምምድ እያደረገ ይገኛል። 'ውድድሩ ከግንቦት 4 እስከ ግንቦት 14 ቀን 2010 ዓ.ም ይካሄል' ተብሎ የታቀደ ቢሆንም የሩዋንዳ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባወጣው መግለጫ አስፈላጊውን የፋይናንስ ድጋፍ ከሴካፋ ባለማግኘቱ ውድድሩን ማራዘሙን አስታውቆ ነበር። በሌላ በኩል ሩዋንዳ ላቀረበችው ጥያቄ ሴካፋ ምላሽ በመስጠቱ ውድድሩ ከግንቦት 10 እስከ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሎ ነበር። ነገር ግን ሴካፋ ለአዘጋጇ አገር ሩዋንዳ ለውድድሩ ዝግጅት መክፈል የሚገባውን ገንዘብ እስካሁን ፌዴሬሽኑ አልሰጠም። በዚህም የተነሳ የሴካፋ ሴቶች እግር ኳስ ውድድር የመካሄዱ ነገር አጠራጣሪ እየሆነ መጥቷል። አዘጋጇ ሩዋንዳን ጨምሮ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ቡሩንዲ እና ጅቡቲ በሴካፋ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ ያሳወቁ አገራት ናቸው። የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) የተለያዩ የአፍሪካ የብሔራዊ ቡድንና የክለቦች ውድድር ለማስተናገድ የፋይናንስ ችግር በስፋት ሲገጥመው ይስተዋላል። ከሁለት ዓመት በፊት ኡጋንዳ ውድድሩን ካስተናገደች በኋላ የሴካፋ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር በበጀት ማጣት ምክንያት መዘግየቱ ይታወሳል። በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን (ሉሲዎች) ከህዳር 8 እስከ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በጋና ለሚካሄደው 11ኛው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ የመጀመሪያ የማጣሪያ መጋቢት 2010 ዓ.ም ከሊቢያ አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ በደርሶ መልስ ውጤት 15 ለ 0 ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል። በጋና በሚካሄደው ውድድር ለመሳተፍ ሉሲዎቹ በቀጣይ ግንቦት 29 ቀን 2010 ዓ.ም ከአልጄሪያ ጋር አልጀርስ ላይ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደርጋሉ። የመልሱን ጨዋታ ደግሞ ሰኔ 3 ቀን 2010ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያካሄድ ይሆናል። ለዚህም ጨዋታ ሉሲዎቹ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
5321
 
1606
 
969
 
215
 
9052
 
822
 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም