በምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ በትራፊክ አደጋ የአራት ሰዎች ህይዎት አለፈ

90
አዳማ ነሀሴ 16/2010 በምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ዛሬ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉን የዞኑ ፖሊስ አስታወቀ፡፡ የዞኑ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው አለሙ ለኢዜአ እንደገለፁት ዛሬ ከንጋቱ 11፡30 ላይ አደጋው የደረሰው በወረዳው ቆቃነጌዎ ቀበሌ አሸዋ ጭኖ ከሙገር ወደ ሃዋሳ በመጓዝ ላይ የነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 - 75294 ኢት ትራከር የጭነት መኪና አራት ሰዎችን አሳፍሮ ከአርሲ ነገሌ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ ከነበረ ኮድ 3 -ኤ48809 ኢት ፒካኘ መኪና  ጋር በመጋጨቱ ነው፡፡ በአደጋው በፒካኘ መኪናው ውስጥ ተሳፍረው የነበሩት አራቱም ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ  ማለፉን ተናግረዋል፡፡ የአደጋው መንስኤ እየተጣራ ሲሆን ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አሽከርካሪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው  ኮማንደር አስቻለው አለሙ አሳስበዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዚሁ ዞን አድአ ወረዳ አቢ ቀበሌ ውስጥ ትናንት ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ የጣለውን ሃይለኛ ዝናብ ተከትሎ በወረደ መብረት ዝናቡን ለማሳለፍ ዛፈ ስር ተጠልለው ከነበሩት ሁለት ወንድማማቾች መካከል የአንደኛው ህይወት ወዲያውኑ አልፏል፡፡ በአደጋው ህይወቱ ያለፈው ታናሽ ወንድም ደግሞ  በመብረቁ ከባድ ጉዳት ደርሶበት በቢሾፍቱ ከተማ በህክምና ላይ እንደሚገኝ ጨምረው ገልፀዋል፡፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም