ለአፋር ሕዝብ ጠላትን የሽንፈት ካባ ማከናነብ አኩሪ የጀግንነት ባሕሉ ነው

163

ህዳር 17/2014 (ኢዜአ) ለአፋር ሕዝብ ጠላትን የሽንፈት ካባ አከናንቦ መመለስ ጥንትም የነበረ አኩሪ የጀግንነት ባሕሉ ነው ሲሉ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሙሳ አደም ገለጹ፡፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሰርጎ በገባባቸውና ወረራ በፈጸመባቸው የአፋር አካባቢዎች የፀጥታ መዋቅሩና ሕዝቡ ባደረጉት የተቀናጀ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ሠብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሶበት ወደ መጣበት ተመልሷል።

የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሙሳ አደም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአፋር ሕዝብ ከህወሓት ጋር እያደረገ ባለው ራስን የመከላከል ጦርነት አንጸባራቂ ድል እያስመዘገበ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የአፋር ሕዝብ ሰላም ወዳድ ነው ያሉት አቶ አደም ሊወረው የመጣን ጠላት ግን አሳፍሮና የውርደት ካባ አከናንቦ መመለስ ጥንትም የነበረ አኩሪ የጀግንነት ባሕሉ ነው ብለዋል፡፡

ድል ያለ መስዋዕትነት እንደማይገኝ የአፋር ሕዝብ ጠንቅቆ ያውቃል፤ ለዚህም አስፈላጊውን ሁሉ እየከፈለ ወረራውን እየመከተ ይገኛል ነው ያሉት።

ድል ሁሌም ከሃቀኞች ጎን በመሆኑ እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ የአፋር ሕዝብም በአሸባሪው ህወሓት እብሪት ተገዶ በገባበት ጦርነት በወራሪው ላይ ድል እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል፡፡

አቶ ሙሳ የአፋር ሕዝብ ከአባቶቹ የወረሰው 'ዳጉ' የተሰኘው ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ ባሕል ያለው መሆኑም ሌላው የድሉ ምስጢር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የሕዝቡ ማኅበራዊ ስሪት በትንሹ የማይበረግግና ለጠላት የማይመች እንደሆነም ነው የገለጹት።

የአፋር ሕዝብ ቀዳሚ ምርጫ ሠላም ነው ያሉት አቶ ሙሳ፤ ህወሓት የማን አለብኝ እብሪቱን የሚቀጥል ከሆነ እስከመጨረሻው ለመታገል ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም