የአደስ አበባ ከተማ ትምህርት ማህበረሰብ 50 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረጉ

59

ደብረብርሃን ህዳር 16/2014  በአደስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች 50 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ለሀገር መከላከያ ሠራዊትና በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች ዛሬ አደረጉ ።

በአሸባሪው ህወሓት የተጋረጠውን ወቅታዊ የሕልውና አደጋ በአጠረ ጊዜ ለመቀልበስ እየተካሄደ ላለው ሁሉን አቀፍ ትግል ስኬት የአደስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።

በአደስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማእረግ የማዘጋጃቤታዊ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ጥረቱ በየነ በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ እንደገለጹት የአሸባሪውን ህወሓት ሀገር የማፍረስ  እኩይ ዓላማ ለማምከን የከተማ አስተዳደሩ ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር በቁርጠኝነት እየሰራ ነው።

የአደስ አበባ ማህበረሰብ ልጆቹን መርቆ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀሉ ከመላክ ባሻገር ያልተቋረጠ የስንቅና ትጥቅ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

እንዲሁም በአማራና አፋር ክልሎች አሸባሪው ህውሓት በፈጸመው ወረራ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎችን ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

በዛሬው ዕለትም የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ማህበረሰብ 50 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ፣ አልባሳትና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉንም ተናግረዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ወልደአማኑኤል እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት በፈጸመው ወረራ ከሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች የተፈናቀሉ ከ300 ሺህ በላይ ወገኖች በዞኑ የተለያዩ ጊዜያዊ ጣቢያዎች ይገኛሉ።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ማህበረሰብ የተፈናቃይ ወገኖቹን ችግር በመገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ከማጠናከሩም ባሻገር የተፈናቃዮችን ስነልቦና ለመገንባት ፋይዳው ከተፍተኛ ነው።

ይህ አስቸጋሪ ወቅት እስኪያልፍ ሌሎች ድርጅቶች፣ ተቋማትና ማህበረሰቦች ተመሳሳይ ድጋፍ በማድረግ የወገኖቻቸውን ችግር እንዲጋሩ አቶ ሲሳይ ጥሪ አቅርበዋል።

የደሴ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ ገብረመስቀል በዚሁ ጊዜ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው ባስተላለፉት መልዕክት  የሽብር ቡድኑን በመቅበር የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ የማቋቋም ስራ ይሰራል ብለዋል።

ከኢትዮጵያዊያን እስካሁን በችግሩ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ወገኖች የተደረገው ድጋፍ የሚበረታታ በመሆኑ ይኸው ድጋፍ  በመልሶ መቋቋም ስራውም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም