በሎስ አንጀለስ የሚኖሩ አስር ጓደኛሞች በአፋር ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

66

ህዳር 16/2014 (ኢዜአ) በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ የሚኖሩ አስር አገር ወዳድ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጓደኛሞች በአፋር ክልል አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ አደረጉ፡፡

ድጋፉ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ በኩል ለተጎጂዎቹ እንደሚደርስ ተገልጿል።

አስሩ ጓደኛሞች ያደረጉትን ድጋፍ በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃደኛ አስተባባሪ የሆኑት ወይዘሮ ሔለን አይችሉህም ሰመራ ዩኒቨርሲቲን ተወካይ አቶ ሙሳ አደም አስረክበዋል፡፡

ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ በራሳቸው ተነሳሽነት ያደረጉት ድጋፍ በጦርነቱ ምክንያት ከሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች እንደሚውል ወይዘሮ ሔለን ተናግረዋል።

ጓደኛሞቹ ኢትዮጵያን ከተጋረጠባት አደጋ ለመታደግ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የእራት ግብዣ አዘጋጅተው ገንዘቡን ማሰባሰባቸውን ገልጸዋል።

የድጋፉ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቴዎድሮስ ማሞ ከአሜሪካ በቪድዮ ባስተላለፉት መልዕክት አሸባሪው ህወሓት በአፋር ክልል ጋሊኮማ በንጹሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ መፈጸሙን አስታውሰዋል።

የሎስ አንጀለሶቹ ጓደኛሞችም ከዚህ ጭፍጨፋ የተረፉት ወገኖች በችግር ውስጥ መሆናቸውን በመረዳት "የበኩላችንን ለመወጣት ወስነን ወደ እንቅስቃሴ ገብተናል" ብለዋል፡፡

በዚህም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር /ከ25 ሺህ ዶላር/ በላይ በማሰባሰብ ዱቄት፣ ዘይት፣ ፓስታ፣ የቤት ቁሳቁስ እና የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ በመግዛት ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

ድጋፉን ሰመራ ዩኒቨርሲቲን ወክለው የተረከቡት አቶ ሙሳ አደም ለጓደኛሞቹ ምስጋና አቅርበው ይህ መልካም ተግባራቸው እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ሌሎችም የእነርሱን ፈለግ በመከተል ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማገዝ በሚደረገው ርብርብ የበኩላቸውን ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም