ኢትዮጵያን ለመበታተን የመጣው ባንዳ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቆራጥ አመራር ይመከታል

241

ህዳር 16/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለመበታተን የመጣው ባንዳ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቆራጥ አመራርና በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ እንደሚመከት በካራማራ ጦርነት ገድል የፈፀሙት ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ ተናገሩ።

የቀድሞ ሰራዊት የጦር መኮንኖች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፈለግ ተከትለው ወደጦር ግንባር መዝመታቸው ጦርነቱን በአጭር ጊዜ በስኬት ለማጠናቀቅ የሚያስችል መሆኑንም ገልፀዋል።

ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ የሶማሊያ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጦ የካራማራ ኮረብታዋችን ጨምሮ የተለያዩ ቦታዎችን በወረረ ጊዜ በጦር ግንባር ተሰልፈው ጀብዱ ከፈፀሙ የአገር ባለውለታዎች አንዱ ናቸው።

ሶማሊያ ወረራውን ባካሄደችበት ወቅት የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ኅይለማርያም ያቀረቡትን የእናት አገር ጥሪ ተቀብለው ነበር ሻለቃ አሊ በርኬ ታጠቅ ማሰልጠኛ ጣቢያ የገቡት።

ሻለቃ ባሻ አሊ በካራማራ በተደረገው ውጊያ በቦንብ ታንክ ማርከዋል፤ ለዚህም ተግባራቸው ከጦርነቱ በኋላ የጦር ሜዳ ጀብዱ ኒሻን ተሸልመዋል።

በወቅቱ ኢትዮጵያ ድል የተጎናጸፈው ህዝቡ ሁሉ "እናት አገር  ወይም ሞት" ብሎ በመትመሙ መሆኑን ሻለቃ ባሻ አሊ ገልፀዋል።

ሶማሊያ በበርካታ አገራት ታግዛ ጦርነቱን ብታካሂድም በተባበረ የኢትዮጵያዊያን ክንድ መመከቱን አስታውሰው አሁንም በምዕራባውያን እየታገዘ ጦርነት የከፈተው ጁንታ ሽንፈት መከናነቡ አይቀሬ ነው ብለዋል።    

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደግንባር መዝመት የአሸባሪውን ቡድን እድሜ እንደሚያሳጥረውና ኢትዮጵያዊያንም ይህን ባንዳ ቀብረው ወደ ልማት ስራዎቻቸው እንደሚመለሱ አልጠራጠርም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም