የራሱን ፍላጎት ለማሳካት በዲሞክራሲ ስም ሌሎችን እንዲጫን የተፈቀደለት አገር የለም

100

ህዳር 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) “ዴሞክራሲ የሁሉም የሰው ልጆች የጋራ እሴት እንጂ በጥቂት አገራት ባለቤትነት የሚያዝ አይደለም” ስትል ቻይና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባዩዋ ዋንግ ዌንቢን በኩል አስታወቀች፡፡

ቻይና ዴሞክራሲን በባለቤትነት እንዲይዝ የተፈቀደለት ብቸኛ አገር የለም በማለት የአሜሪካንን በዴሞክራሲ ሽፋን በአገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ የምታደርገውን ጣልቃ ገብነት እንደምታወግዝ በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች፡፡

ቃል አቀባዩ አክለውም አሜሪካ የዴሞክራሲ ሽፋንን የጂኦ ስትራቴጂክ ፍላጎቷን ለማሳካት፣ ሌሎች አገራት ላይ ጫና ለማሳደር፣ ዓለምን ለመከፋፈል እና የራሷን አጀንዳ ማስፈጸሚያ መሳሪያ አድርጋዋለች ብለዋል፡፡

አሜሪካ የአንድ ቻይና መርህን በሚጻረር መልኩ ታይዋንን ነጻ አገር እናደርጋለን ለሚሉ አካላት የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቆምም ጠይቀዋል፡፡

በዚህም አሜሪካ በቅርቡ በምታዘጋጀው በዴሞክራሲ ዙሪያ የሚመክር መድረክ ላይ የታይዋን አመራሮችን እንዲሳተፉ መጋበዟን በተመለከተ ቻይና አጥብቃ እንደምትቃወመው ቃል-አቀባዩ ተናግረዋል።

በዴሞክራሲ ስም እየተደረገ ያለውን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ እንቅስቃሴ አውግዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም