ሴቶች በጦርነት ወቅት የእልህ መወጫና የሽንፈት ማገገሚያ ሊሆኑ አይገባም

63

አዲስ አበባ፣ ህዳር 16/2014 /ኢዜአ/ ሴቶች በጦርነት ወቅት የእልህ መወጫና የሽንፈት ማገገሚያ ሊሆኑ አይገባም ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቀ ዘውዴ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቷ ለ16 ቀናት በተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚካሄደውን የጸረ-ፆታዊ ጥቃት ዘመቻ አስጀምረዋል።

አሸባሪው ህወሓት በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በከፈተው ጦርነት በርካታ ሴቶች፣ ሕፃናትና አረጋዊያን አሰቃቂ ፆታዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ፆታዊ ጥቃት ደርሶባቸው በሕክምናና በማገገሚያ ማዕከላት የሚገኙ በርካታ ህፃናት፣ ሴቶችና አረጋዊያንን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

በጦርነት ወቅት ሴቶችን የእልህ መወጣጫ የማድረግ አካሄድ ሊቆም ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

ችግሩ አስከፊ በመሆኑ ፆታዊ ጥቃትን የመከላከልና የማስቆሙ ተግባር የአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን የሙሉ ጊዜ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በፆታዊ ጥቃት ሳቢያ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ሁሉም በሃላፊነት ሊንቀሳቀስ ይገባልም ብለዋል።

የ16 ቀናት የፀረ ፆታዊ ጥቃት ዘመቻው "ሠላም ይስፈን፤ በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚደረግ ፆታዊ ጥቃት ይቁም" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የሚካሄደው።

በዘመቻው ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መአዛ አሸናፊ፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም