በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በደራሽ ጎርፉ ተውጠው የነበሩ 21 ሰዎችን ከጉዳት ማዳን ተቻለ

60
አዲስ አበባ  ነሀሴ 16/2010 በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በተለምዶ አቃቂ መሿለኪያ ድልድይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ዛሬ ማለዳ የደራሽ ጎርፍ አደጋ ተከስቶ በውሃ ተውጠው የነበሩ 21 ሰዎችን ህይወት መታደግ መቻሉን የከተማው የእሳትና ደንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን አስታወቀ። የባለስልጣኑ የኮሙኒዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ስለሺ ተስፋዬ እንዳሉት በውሃ ተከበው የነበሩት 21 ሰዎች የቸራልያ ምግብ ማቀነባበሪያ ሰራተኞቸ ናቸው። ሰራተኞቹ ወደስራ ለመግባት በመስሪያ ቤቱ አውቶብስ (ሰርቪስ) እየተጓዙ ሳለ ነበር ጎርፍ ባስከተለው ሰፊ ኩሬ የተያዙት። በውሃ ከተዋጠው አውቶብስ በመውጣት በተሽከርካሪው አናት ላይ ሆነው የድረሱልኝ ጥሪ ሲያሰሙ እንደነበር የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው ተናግረዋል። ድንገተኛ ጎርፉ ተውጠው የነበሩ 21 ሰዎችን ይህወት መታደገ የተቻለው በሄሊኮፕተርና በከባድ ክሬን በመታገዝ በተካሄደው የህይወት ማዳን ተግባር ነው። ባለስልጣኑም በደረሰው ጥሪ መሰረት የአደጋውን ክብደት ከተመለከተ በኋላ ከአገር መከላከያ ሚኒስቴር  ሄሊኮፕተር፤ ከዋልያ ቢራ ፋብሪካ ደግሞ ክሬን በመዋስ የህይወት አድን ተግባሩን አከናውኗል። በዚሁ ተግባር ውኃ ጠላቂ የነፍስ አድን ባለሙያዎች እና ከባድ ተሽከርካሪዎችን ተጠቅሟል። ሰራተኞቹ  ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው ነው እንዲወጡ ማድረግ የተቻለው። በአካባቢው በተከሰተው ደራሽ ጎርፍ የትራንስፖርት አገልግሎት መስተጓጎል ማስከተሉንም አቶ ስለሺ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም