ኢትዮጵያውያንም የዓድዋን ታሪክ እንደሚደግሙ አንጠራጠርም- አረጋዊያን ማህበር

82

ባህር ዳር ህዳር 15/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን ከመሪያቸው ጎን በመሆን የእድዋን ታሪክ እንደሚደግሙ አንጠራጠርም ሲሉ የአማራ ክልል አረጋዊያን ማህበር አባላት ገለጹ ።
ኅብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ሀገር የማዳን ተግባሩን ከመሪው ጎን ተሰልፎ እንዲያጠናክር አረጋዊያኑ ጥሪ አቅርበዋል።

የማህበሩ አባላት ኢዜአ እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ሀገርን በመሥዋዕትነት መምራት የሚያስፈልግበት ጊዜ በመሆኑ የሕልውና ዘመቻውን በግንባር ለመምራት መዝመታቸው ብዙዎችን ያነሳሳል።

ከአባላቱ መካከል ሃምሳ አለቃ ንጉሴ ዳኛው እንዳሉት ደከተር ዐቢይ "እኔ ወደትግል ሜዳ እዘምታለሁ ሌሎችም ለሀገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሱ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ'' ማለታቸው በሀገራቸው ጉዳይ የማይደራደሩ መሪ መሆናቸውን በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል።

"ታሪክ ራሱን ደገመ ማለት ይቻላል" ያሉት ሃምሳ አለቃ ንጉሴ፣ ከዚህ በፊት ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ለመውረር በሞከሩበት ወቅት ዳግማዊ ዓፄ ሚኒልክ ተመሳሳይ ተግባር መፈጸማቸውን አስታውሰዋል።

በወቅቱ ለሕዝባቸው ያቀረቡት የክተት ጥሪና እሳቸውም በጦርነቱ ከፊት መሰለፋቸው ወራሪውን ኃይል በመመከት ኢትዮጵያን ለድል አብቅቷል።

"አሁንም በልጆቿ ጀግንነትና መሥዋዕትነት ክብሯንና ነፃነቷ ተጠበቆ የቆየው ኢትዮጵያ ነፃነቷን አሳልፎ ላለመስጠት ጠቅላይ ሚኒስትራችን በግንባር መሰለፋቸው ለብዙዎቻ ብርታት ነው" ብለዋል።

ለውጭ ኃይሎችና ለውስጥ ባንዳዎች ድንጋጤን ከመፍጠሩም በላይ መልዕክት የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሃምሳ አለቃ ንጉሴ እንዳሉት የኢትዮጵያ ህዝብ መሪው ከፊት ሁኖ እያዋጋው ይቅርና ከቤተመንግስት ሁኖ በሚናገረው ንግግር ብቻ ትዛዙን የሚፈጽም ቀናኢ ህዝብ ነው።

መንግስት በትግስት ብዙ ነገር ቢያሳልፍም በአንዳንድ ምዕራባዊያንና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሚጋለበው አሸባሪው ህወሓት ከጠላት ጋር አብሮ ሀገር ከማፍረስ ተግባሩ እንዳልተቆጠበም ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደግንባር መዝመት ችግሩን ፈጥኖ ለመቀልበስ ከሚኖረው ፋይዳ ባለፈ ለቀጣይ ትውልድም ዓርዓያነት የሚኖረው ነው ብለዋል።

ዓፄ ሚኒልክ ህዝብን አስተባብረው ኢትዮጵያን ከወራሪ ኃይል እንደታደጉ ሁሉ ዛሬም የኢትዮጵያ ሕዝብ መሪውን ያሳፍራል የሚል ፅኑ እምነት የለንም ብለዋል።

"ጠቅላይ ሚኒስትራችን በግንባር ተሰልፈው የዳግማዊ ዓፄ ሚኒልክን ታሪክ እንደደገሙ ሁሉ ኢትዮጵያዊንም ከመሪያቸው ጋር በመሆን የአድዋን ታሪክ እንደሚደግሙ አልጠራጠርም" ሲሉም አክለዋል።  

"የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ለፀጥታ አካላት ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡም የማሸነፍ ሞራል እንዲሰንቅ ያደርገዋል" ያሉት ደግሞ የማህበሩ የቁጥጥር ኮሚቴ ፀሐፊ አቶ አበበ ይልማ ናቸው።

"የውክልና ጦርነት እያካሄደ ያለውን የአሸባሪውን ህወሓት አከርካሪ ለመስበር እንዲህ አይነት ቆራጥ ውሳኔ ያስፈልጋል'' ያሉት አቶ አበበ፣ የጠቅላይ ሚንስትሩ ውሳኔ ከመዘግየቱ በስተቀር ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጦር ግንባር በመሰለፍ አመራር ሰጥተው ይቅርና በአንዳንድ አውደ ግንባሮች ሠራዊቱን ሲያነቃቁ ከፍተኛ ድል መገኘቱን አስታውሰዋል።

ኅብረተሰቡ በተለይ ወጣቱ በአሁኑ ወቅት ከመሪው ጎን በመሰለፍ ሁሌም ታሪክ የሚዘክረው ተጋድሎ መፈጸም እንዳለበት አመልክተዋል።

"የጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባር መዝመት ሁሉንም ስለሚያነሳሳ ጦርነቱን በድል አድራጊነት ለመቋጨት የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል" ሲሉም አቶ አበበ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም