የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የመኖርና ያለመኖር አደጋ የተደቀነበት በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትራችንን መከተል አለብን

84

አዲስ አበባ፣ ህዳር 15/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የመኖርና ያለመኖር የህልውና አደጋ የተደቀነበት በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትራችንን መከተል ይኖርብናል ሲል ታዋቂው አርቲስት ጸጋዬ እሸቱ ተናገረ።

አርቲስት ጸጋዬ እሸቱ ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታ፤ አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት ኢትዮጵያን የሚያዩበትና የሚከታተሉት መንገድ የተሳሳተ እንደሆነ ይናገራል።

አውሮፓዊያኑ የኢትዮጵያን ደማቅ ታሪክ ለማደብዘዝ እንዲሁም ለማጉደፍ በርካታ ጥረቶችን የሚያደርጉ መሆኑንም ገልጿል።

ይህ ብቻ አይደለም በኢትዮጵያ ትውልዱ እምነት አልባና ታሪክና ማንንቱን የማያውቅ እንዲሆን ብዙ ተሰርቷል ይላል።

በዚህ አላበቁም ዓላማቸው በሚፈልጉት ልክ ሊሳካ ባለመቻሉ ለረጅም ዘመናት አጥንተው ሁሉ ነገር ቅኔ የሆነችባቸውን አገር ለማፍረስ እየሰሩ መሆኑን አርቲስት ፀጋዬ እሸቱ ይናገራል።

የኢትዮጵያ ጠላቶች የያዙትን እኩይ ዓላማ ጠንቅቀው የሚያውቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ ወደ ግንባር ዘምተዋል።

"ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ፤ ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለአገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሱ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ!" ማለታቸው ይታወቃል።

መሆኑም አሁን ላይ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የመኖርና ያለመኖር የህልውና አደጋ የተደቀነበት በመሆኑ ሁላችንም ጠቅላይ ሚኒስትራችንን መከተል ይኖርብናል ብሏል አርቲስት ጸጋዬ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባት ከዘመቱ ልቡ የማይነሳሳ ኢትዮጵያዊ ሊኖር እንደማይችል አምናለሁ ያለው አርቲስቱ የሚችለው በመዝመት ሌላው በመደገፍ አጋርነቱን በማሳየት አለበት ብሏል።

የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ዜጋ መሆን ብቻውን በቂ በመሆኑ "ድል አድራጊነትን ከሌላ ሳይሆን ሁላችንም በራሳችን በማሳካት የድሉ ባለቤት መሆን ይጠበቅብናል ነው ያለው።

ወቅቱ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ የሚመለስበት እንጂ እርስ በእርስ ለመወቃቀስ የሚሆን የባከነ ሰዓት እንኳ ሊኖረን አይገባም ሲልም ተናግሯል።

ዓለም አቀፍ ጫናውንና የከሃዲዎችን የተቀናጀ ጥቃት ለመመከት ሁሉም የበኩሉን አገራዊ ሃላፊነት መወጣት አለበት ብሏል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም