ዩኒሴኤፍ በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች ቀጥታ ድጋፍ የሚውል 110 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታወቀ

100

ባህርዳር፣ህዳር 15/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት ወረራ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለሦስት ወር ለመደገፍ የሚያስችል መርሃግብር ማስፈጸሚያ 110 ሚሊዮን ብር መመደቡን ዩኒሴፍ አስታወቀ።

በቀጥታ ገንዘቡ ድጋፍ የሚደረግበት ይህ መርሃግብር በዩኒሲኤፍ፣ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም በአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ትብብር እንደሚፈጸምም ተመላክቷል።

በተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴኤፍ) የአማራ ክልል አስተባባሪ አቶ አዲሱ ጫኔ መርሃግብሩ ይፋ ሲደረግ እንደገለጹት፣ ለቀጥታ ድጋፍ መርሃግብሩ ገንዘቡ የተገኘው ከስዊድን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ነው።

በመርሃግብሩ ከ45 ሺህ በላይ ለችግር የተጋለጡ ተፈናቃዮችን በመለየት ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራም አመልክተዋል።

አስተባባሪው እንዳሉት ለችግር የተጋለጡ ተፈናቃዮችን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በጥንቃቄ በመለየት ገንዘቡ በባንክ የሒሳብ ቁጥራቸው ገቢ ይደረጋል።

በቀጥታ በሚሰጣቸው ገንዝብ በአይነት ከሚደረግላቸው በተጨማሪ በመሰረታዊነት የሚያስፈልጓቸውን ገዝተው ለመጠቀም ዕድል የሚያገኙበት ድጋፍ መሆኑንም ነው ያስረዱት።

ድርጅታቸው በአጣዬ ከተማ የፀጥታ ችግር ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ በክልሉ ከ73 ሚሊዮን ብር ባለይ በመመደብ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህን ለማጠናከር በአሁኑ ወቅትም 33 ሚሊዮን ብር ለመመደብ በሂደት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

አቶ አዲሱ እንዳሉት በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሓት በክልሉ በፈጸመው ወረራ የደረሰውን ሰብአዊ ቀውስ ለማቃለል ድርጅቱ የድርሻውን እየተወጣ ነው።

የቀጥታ ድጋፍ መርሃ ግብሩ ዛሬ ይፋ ሲደረግ ድርጅቱ ሁለት መኪና ደረቅ እና የህጻናት አልሚ ምግብ እንዲሁም ፍራሽና ሌሎች ቁሶችን ለተፈናቃዮች ደግፏል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ መርሃግብሩ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ይፋ ሲደረግ እንደገለጹት፣ አሸባሪው ህወሓት በፈጸመው ወረራ በዜጎች ላይ ሰብዓዊና ማህበራዊ ቀውስ ተፈጥሯል።

በወረራው ተፈናቅለው በችግር ውስጥ የሚገኙ ሴቶች፣ ህጻናትንና አረጋውያንን በልዩ ትኩረት ለመደገፍ ከዩኒሴአፍ ጋር በመተባበር የቀጥታ ድጋፍ መርሃግብሩ ይፋ መደረጉንም አስታውቀዋል።

ለሦስት ወር በሚቆየው ለእዚህ መርሃግብር ዩኒሲኤፍ 110 ሚሊዮን ብር መመደቡን ጠቁመው፣ "ገንዘቡ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በአጋር አካላት ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል" ብለዋል።

ይህም ተፈናቃይ ወገኖች በቁሳቁስ እና በአይነት ከሚደረግላቸው ድጋፍ ባሻገር በሚሰጣቸው ገንዘብ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።

በአማራ ክልል በአጠቃላይ ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው እንደሚገኙ ከክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም