አሸባሪውን ሽኔን ለመደምሰስ በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን የጉጂና ጌዴኦ ዞኖች አስታወቁ

109

ዲላ ህዳር 15/2014 (ኢዜአ) የአሸባሪው ሽኔ ታጣቂዎችን የጥፋት ለመደምሰስ በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ምዕራብ ጉጂና ጌዴኦ ዞኖች አስታወቁ።
የሁለቱ ዞኖች የአስተዳደርና የፀጥታ አካላት የአጎራባች ወረዳዎች ሰላምን በዘላቂነት ለማስጠበቅና በቀጣይ ጊዜያት በሚሰሩ በፀጥታ ሥራዎች ዙሪያ ዛሬ በዲላ ከተማ መክረዋል።

በመድረኩም ከአካባቢው ፀጥታ አካላት ባለፈ ህዝባዊ ሠራዊቱንም በማቀናጀት የአሸባሪውን ተላላኪ ቡድን መቀመጫ ለማሳጣት የጋራ አቋም መያዙ ተጠቁሟል ።

በመድረኩ ማጠቃለያ የምዕራብ ጉጂ ዞን ሚሊሻ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ቁጡ እንዳሉት የአሸባሪው ሸኔ ታጣቂዎች በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የሐሰት መረጃ በመንዛት ህዝቡን እረፍት እየነሱት ነው።

ሆኖም የዞኑ ፀጥታ አካለት በሽብር ቡዱኑ ላይ የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ጠቅሰው ኅብረተሰቡም አካባቢውን በንቃት መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በተለይ በውስጣችን ሆነው የሚንቀቀሱ የአሸባሪው ቡድን ተላላኪዎችን በማጋለጥና ለሀሰት መረጃ ቦታ ባለመስጠት ኅብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ አሳሰበዋል።

በምዕራብ ጉጂ ዞን መንቀሳቀሻ ሲያጡ ንጹ መስለው በጌዴኦ ዞን የሚቀሳቀሱትን የቡዱኑ አባላት አሳልፎ በመስጠቱ ረገድ ከጌዴኦ ዞን ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከሩንም ገልጸዋል።

የጌዴኦ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ሃላፊ አቶ አበባዬሁ ኢሳያስ በበኩላቸው የአሸባሪውን ህወሓት የውሸት የድል ዜናን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአጎራባች አካባቢዎች ወጣ ገባ የሚለውን አሸበሪውን ሼኔን ለማጽዳት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን  አስታውቀዋል።

የአሸባሪውን እንቅስቃሴ በመከታተል ተገቢውን እርምጃ ለመውስድ የመረጃ ልውውጥ ከማድረግ ባለፈ ርዝራዦችን የማደኑ ስራ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ  መሆኑን  አመልክተዋል።

የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ከማጠናከር በተጓዳኝ ሕዝባዊ ሠራዊቱን በማቀናጀት አሽበሪውን ቡድን መቀመጫ  ለማሳጣት  በሁለቱ ዞኖች  የተጀመረው  የቅንጅት  ስራ  ተጠናክሮ  እንዲቀጥል  መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

በዚሁ ለአንድ ቀን በተዘጋጀው የጋራ ውይይት መድረክ የሁሉቱ ዞኖች የአስተዳደር አካላት፣ የፍትህና የፀጥታ ጽህፈት ቤት የስራ ኃላፊዎች  ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም