በትምህርት ዘርፍ ላይ ያለውን ስር የሰደደ ችግር በጋራ በመፍታት የኢትዮጵያን መፃኢ እድል ማስተካከል አለብን

81

ህዳር 15 ቀን 2014(ኢዜአ) በትምህርት ዘርፍ ላይ ያለውን ስር የሰደደ ችግር በጋራ በመፍታት የኢትዮጵያን መፃኢ እድል ማስተካከል አለብን ሲሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች ከሰው ሃብት ልማት ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላት ጋር የትውውቅ መድረክ አካሂደዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ በዚህን ወቅት በትምህርት ዘርፉ ላይ ዘመናትን ያስቆጠሩ ችግሮች መናራቸውን ተናግረዋል፡፡

የመምህራንና የትምህርት አስተዳደር አቅም ውስንነት፣ ኩረጃ፣ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንዲሁም በዘርፉ ያለው ሌብነት እና አድሏዊ አሰራር  ከችግሮቹ  መካከል ዋናዋናዎቹ  መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በተለይ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚጠበቅባቸውን ደረጃ አለማሟላትም ሌላኛው የዘርፉ ማነቆ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በርካታ ትምህርት ቤቶች በአሸባሪው ህወሃት መውደማቸው ደግሞ ችግሩን እንደሚያባብሰው ተናግረዋል፡፡

ይህም ዘርፉ የታለመለትን ግብ እንዳያሳካ ከማድረጉም በላይ አገር ተረካቢ ትውልድ የማፍራት ተልዕኮ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደሩን ነው ያብራሩት፡፡

በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማት ላይ ጉዳት ማድረሱንም እንዲሁ፡፡

ገንዘብ ያላቸው ጥቂት ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ከመንግስት ትምህርት ቤት ይልቅ የተሻሉ ባሏቸው የግል ትምህርት ቤቶች እንደሚያስተምሩና ልጆቻቸውም ከአገራቸው ይልቅ በውጭ አገራት ለመኖር የሚናፍቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተቃራኒው የመንግስት ትምህርት ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ክፍተት መኖሩን የሚናገሩት ሚኒስትሩ፤ ይህም ኢትዮጵያን የማገልገል ውጥን ይዞ የሚያድግ ትውልድ ማፍራት ላይ እንከን መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም ዜጋ ለማዳረስ በጋራ መስራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ለዚህም በትምህርት ስረዓቱ ውስጥ የሚታዩ የብቃት ማነስ፣የጎጠኝነት አመለካከት፣የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት፣ሙስናና ተያያዥ ችግሮችን መታገል የሁሉም ተቋማትና ዜጎች ኃላፊነት መሆኑንም አስታውቀዋል።

ሰው ሃብት ልማት ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው  ቋሚ ኮሚቴው አስፈላጊን ድጋፍና ክትትል ለማድረግ  ችግሮቹን ከግምት ያስገባ  እቅድ ማቀዱን ገልፀዋል።

የችግሮቹን ስፋትና ጥልቀት በመገንዘብና በትብብር መስራት ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተጠቀሱትን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል አሰራር መዘርጋት እንደሚቻልም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም