በቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ ለተጎዱ እንስሳት ከ200 ሺህ በላይ እስር የሳር መኖ ተሰባስቧል

61

ህዳር 15/2014(ኢዜአ) በቦረና ዞን በተከሰተው የድርቅ አደጋ የተጎዱ እንስሳትን ለመታደግ ከኦሮሚያ ክልል፣ ከግልና ከመንግሥት ተቋማት ከ200 ሺህ በላይ እስር የሳር መኖ መሰብሰቡ ተገለጸ።

"ኢትዮጵያዊያን ለኢትዮጵያዊያን አለኝታ ናቸው" በሚል በኦሮሚያ ክልል የፊንፊኔ ዙሪያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በዞኑ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እያሰባሰበ ይገኛል።

ምክር ቤቱ በቦረና ዞን የተከሰተው ተፈጥሯዊ የድርቅ አደጋ እና የከብቶች እልቂት እያስከተለ ያለውን ጉዳትና የድጋፍ አሰባሰብ አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንትና የእርዳታ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኤልያስ ጉዮ  ችግሩን ለማቃለል ሁሉም ዜጋ ባለው አቅም እንዲረባረብና ካለው ላይ እንዲያካፍል ጠይቀዋል።

የድርቁ መንስኤ በዞኑ በየዓመቱ የሚጥለውና 70 በመቶ የሚሆነውን ስርጭት የሚሸፍነው በአካባቢው አጠራር "ገና" የሚሰኘው ዝናብ ከመጋቢት 15 ቀን 2013 ጀምሮ አለመዝነቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ በአካባቢው 30 በመቶውን የዝናብ መጠን የሚሸፍነውና "ሀገያ" እየተባለ የሚጠራው ዝናብ ከመስከረም 15 ጀምሮ አለመዝነቡ ለችግሩ መባባስ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል።

ችግሩን ለመፍታት በቀጣዮቹ አራት ወራት ከባለሃብቶች እና በውጭ አገራት ከሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በድርቁ ሳቢያ በአካባቢው ከ70 ሺህ በላይ እንስሳት መሞታቸውን የኦሮሚያ ክልል መስኖ ልማት ቢሮ የጥናትና ምርምር ቢሮ ኃላፊ አቶ ከተማ ኡርጎ ተናግረዋል።

የተጎዱትን እንስሳት ለመደገፍ የኦሮሚያን ክልል ጨምሮ በርካታ የመንግሥት እና የግል ተቋማት ከ200 ሺህ  በላይ እስር የሳር መኖ መሰብሰቡንም ገልጸዋል።

ከዞኑ የተውጣጡ አባገዳዎች እና አርብቶ አደሮች እንስሳቱን ከድርቅ አደጋ ለመታደግ ሁሉም የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም