ሆስፒታሉ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ያሰባሰበውን ድጋፍ በግንባር ተገኝቶ እንደሚያስረክብ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ሆስፒታሉ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ያሰባሰበውን ድጋፍ በግንባር ተገኝቶ እንደሚያስረክብ ገለጸ
59
አዲስ አበባ ህዳር 15/2014 (ኢዜአ) የቅዱስ አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለአገር መከላከያ ሰራዊት ያሰባሰበውን ድጋፍ በግንባር ተገኝቶ እንደሚያስረክብ ገለጸ።
የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ልዩ አማካሪ መኮንን አስፋው፤ የሆስፒታሉ ሠራተኞች ለመከላከያ ሠራዊት የተለያዩ ድጋፎች ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ሰራተኞች የአንድ ወር ደሞዛቸውን መለገሳቸውን ጠቁመው በተለያዩ ጊዜያት የደም ልገሳ መርኃ ግብር ላይ መሳተፋቸውንም አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ለመከላከያ ሠራዊትና ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው አልባሳትና ደረቅ ምግቦችን ማዘጋጀታቸውን ገልጸው በቀጣይ ግንባር ድረስ በመሄድ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም ለሰራዊቱ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የሆስፒታል ሠራተኞች ለጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ በማድረጋቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ለሰራዊቱ ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ ለአገራቸው ህልውና በመዝመት መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
የሆስፒታሉ ሃኪሞች ግንባር ድረስ በመሄድ ሙያዊ እገዛ ለማድረግ የተዘጋጁ ሲሆን ተፈናቃዮች ባሉበት አካባቢም የህክምና አገልግሎት እንሰጣለን ብለዋል።