በአዲሱ በጀት ዓመት የታቀደውን ገቢ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮች እየተዘረጉ ነው

102
አዲስ አበባ ነሀሴ 16/2010 የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በተያዘው በጀት ዓመት የሚጠበቅበትን ገቢ በብቃት ለመሰብሰብ የሚያስችለውን አዳዲስ አሰራር እየዘረጋ መሆኑን አስታወቀ። በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች የሚታገዙት አዲሶቹ አሰራሮች በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች በሙከራ ደረጃ ሥራ መጀመራቸውን በመጠቆም። የኢትዮጵያ መንግስት በተያዘው በጀት ዓመት ለሚያከናውናቸው የተለያዩ ሥራዎች ማስፈፀሚያ 346 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በጀት ያስፈልገዋል። ከዚህ ውስጥም አብዛኛው ማለትም 213 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በኩል ይሰበሰባል ተብሎ የሚጠበቅ ነው። ያም ሆኖ ግን የአገሪቱ ገቢ የመሰብሰብ አቅም ደካማ በመሆኑ የተነሳ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት መንግስት ከግብር እና ታክስ መሰብሰብ የነበረበትን  በርካታ ገንዘብ ሳይሰበሰብ መቅረቱም ይነገራል። ለምሳሌ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለመሰብሰብ ታስቦ ከነበረው 203 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ የተቻለው 150 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ሲሆን ይህም  የእቅዱን 74 በመቶ ብቻ ነው። የባለስልጣኑ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን ለኢዜአ አንደገለፁት፤ ከገቢ መሰብሰብ አሰራሮች ጋር በተያያዘ የሚታዩ ክፍተቶችን በመሙላትና አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ የሚፈለገውን ገቢ ለመሰብሰብ ሰፊ ሥራ ተጀምሯል። በተያዘው የ2011 በጀት ዓመት መንግስት ለመሰብሰብ ያቀደው ገቢ ከአምናው ጋር ሲነፃፀር 10 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አለው። ይህንን ግብ ማሳካት ይቻል ዘንድ ታዲያ ባለፉት ዓመታት የተስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ጥራት ያለው የግብር አሰባሰብ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀመሯል። በኤሌክትሮኒክስ የሚታገዘው አዲሱ አሰራር ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ለመፍጠርና የማጭበርበር ተግባራትን በመቀነስ በግብር ሰበሳቢውና ከፋዩ ማህበረሰብ መካከል መተማመንን የሚያመጣ መሆኑን ነው አቶ ኤፍሬም የተናገሩት። በተጨማሪም በባለስልጣኑ በኩል ችግር የሆነውን የሰው ኃብት አቅም ማነስ ለመገንባት ለሰራተኛው ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን አቶ ኤፍሬም ገልፀዋል። ባለፈው ዓመት የግብር ማሰባሰብ ተግባራት ላይ ችግር የነበሩት የኦዲትና የህግ ማስከበር ሥራዎች ደካማነትን እንደዚሁም ውዝፍ ታክስን  ተከታትሎ ማስከፈል እንዲታረሙ ትኩረት እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል። ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን የግብር መጠን በታማኝነት አስልቶ አለማሳወቅና ከሽያጭ የሰበሰቡትን ታክስ በጊዜው ለባለስልጣኑ ያለማስገባት ችግሮች እንዳሉባቸውም አቶ ኤፍሬም ጠቅሰዋል። እነዚህን ችግሮች ለመቀነስም ባለስልጣኑ የቅርብ ክትትል ለማድረግ የሚያስችል አሰራር እየዘረጋ እንደሆነ ገልጸዋል። ከዚህም ሌላ ቅሬታ አቅራቢ ግብር ከፋዮች ቅሬታቸው ታይቶ እንዲከፍሉ ውሳኔ የተሰጠባቸውን የገቢ ውዝፎች ቶሎ ገቢ እንዲደረጉ ሁኔታዎች እንደሚመቻቹ ተናግረዋል። በደረሰኝ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ህግ ማስከበር ላይ በተመሳሳይ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራ መሆኑንም ነው የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ የገለፁት። በዚህ ዓመት በአገሪቱ ያለው ፀጥታ መሻሻል ምጣኔ ኃብታዊ እንቅስቃሴው እንዲያንሰራራ ስለሚያደርግ ይኸው ሁኔታ በሚሰበሰበው ገቢ መጠን ላይ በጎ ተፅዕኖ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት የውጪ ምንዛሪ እጥረት ችግሩ እየተፈታ መሆኑን የተናገሩት አቶ ኤፍሬም ይህም በተለያየ የንግድ እንቅስቃሴ አማካኝነት ከውጭ ከሚገቡ እቃዎች የሚገኘውን ገቢ ያሳድገዋል ተብሎ ተስፋ እንደተጣለ ተናግረዋል። ባለስልጣኑ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ወር 14 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ጠቁመዋል። ባለስልጣኑ ከ213 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ የመሰብሰብ ኃላፊነት ሲጣልበት በ2011 በጀት ዓመት ከገቢ ዕቃዎች የሚገኘው ቀረጥ የ9 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት እንደሚኖረውና ይህም ከገቢ ዕቃዎች ለሚሰበሰበው የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ መሰረት መደረጉን በጀቱ ፓርላማ ቀርቦ በፀደቀበት ወቅት መጠቀሱ ይታወሳል። ኢትዮጵያ ለ2011 ካፀደቀችው 346 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ውስጥ 59 ቢሊዮን ብር ያህል ጉድለት መኖሩ የሚታወቅ ሲሆን ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ገቢ የሚሸፍነው እንደሚሆን ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም