ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመታቸው ኢትዮጵያን ያስከበሩ የቀደምት መሪዎችን ታሪክ የደገመ ነው

73

ጋምቤላ ፤ ኅዳር 15/2014(ኢዜአ)ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ግንባር መዝመታቸው ኢትዮጵያን ያስከበሩ የቀደምት መሪዎችን ታሪክ የደገመ መሆኑን የጋምቤላ ክልል አመራሮች ተናገሩ።
ለመከላከያ ሠራዊት ደጀን በመሆንና በአሸባሪው ህወሓት ወረራ የተፈናቀሉትን ዜጎች በመደገፍ ሚናቸውን እንደሚወጡም  ተመልክቷል።

አመራሮቹ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባር ተገኝተው ጦርነቱን ለመምራት ወስነው ወደ ተግባር መግባታቸው ቀደምት መሪዎች የውጭ ወራሪዎችን አሳፍረው የመለሱበትን ታሪክ ዳግም ለማስመዝገብ ያስችላል።  

የጋምቤላ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ኡቦንግ ኡቻላ ፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገር ለማዳን የሚካሄደው ዘመቻውን በግንባር በመገኘት ለመምራት መወሰናቸው ተገቢ ነው ይላሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ የኢትዮጵያን አንድነት በማስከበር ጠላትን አሳፍረው የመለሱትን የቀደምት መሪዎችን  ታሪክ ለመድገም  ያስችላል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን አርአያነት በመከተልም በህወሓትና በውጭ ጠላቶች የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ  እንሰራለንብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  በግንባር ጦርነቱን ለመምራት የደረሱበት ውሳኔ የሕልውና ዘመቻውን እንድቀላቀል የበለጠ አነሳስቶኛል  ያሉት  ሌላው ደግሞ የክልሉ ስፖርት ኮሚሽነር ታይዶር ቻንባንግ ናቸው።  

የህልውና ዘመቻውን በድል ለመቋጨትም መላው ህዝብ ከስንቅ ዝግጅት ጀምሮ አካባቢው በመጠበቅና በዘመቻው በመሳተፍ የዜግነት ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ኦላን ጋች በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን ሕልውና ለማረጋገጥ የሚፈለግባቸውን መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለመከላከያ ሠራዊት ደጀን በመሆንና በአሸባሪው ህወሓት ወረራ የተፈናቀሉትን ዜጎች በመደገፍ ሚናቸውን እንደሚጫወቱም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም