የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢው እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ላይ እንዲውል እየሰራ ነው

96

ህዳር 14/2014 (ኢዜአ) የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሀገርን ከብተና ለመታደግ እየተካሄደ ያለው የሕልውና ዘመቻ እንዲሳካ ከማገዝ ባሻገር የአካባቢው እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ጥቅም ላይ እንዲውል እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት  ዶክተር  ሰለሞን ዘሪሁን  ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የሀገር ህልውና ለማረጋጋጥ የተጀመረው ዘመቻ ፣ በጦርነት የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም የሚደረጉ ጥረቶች እንዲሳኩ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በእስካሁን ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ለሀገሩ ህይወቱን እየሰጠ ለሚገኘው የሀገር አለኝታ መከላከያ ሠራዊት ማበርከቱን አስታውሰዋል።

እንዲሁም በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖችም 2 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የምግብና የቁስ ድጋፍ አድርጓል፤ ሰሞኑን ተመሣሣይ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቋል ብለዋል፡፡

እንደ ዶክተር ሰለሞን ገለፃ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በተጓዳኝ የድሬዳዋ እምቅ የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ ሀብቶች ለልማት ውለው ሥራ እጥነትን እንዲቃላል የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እያካሄደ ይገኛል፡፡

በዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን፤ ትስስሮቹን በመደገፍ ድሬዳዋ የምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ድሬዳዋ የምትታወቅበትን ጥሬ የሲሚንቶ ሀብቶችና ለግንባታ የሚያገለግሉ ‹‹ጉጉባ›› የሚባለው አፈር በሣይንሳዊ ጥናት ተደግፎ ለሀገር ልማትና ለሥራ ዕድል ማስገኛ እንዲውል የማድረግ ሥራም ተጀምሯል፡፡

የወዳደቁ የፕላስቲክ ኮዳዎች መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ፕሮጀክት ተቀርፆ ሰሞኑን ወደጥናት መገባቱም ጠቁመዋል።

ይህም የተፈጥሮ ሚዛንን ከመጠበቅ ባሻገር ለበርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ድሬዳዋ የምትታወቅባቸውን የጣፋጭ ምግቦቿን ደረጃ ከፍ በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማግኛ እንዲሆኑ ‹ብራንድድ› ተደርገው ወደ ውጭ እንዲላኩ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር ኡባህ አደም በበኩላቸው ዩኒቨርሲው የሀገር ሕልውና ለማረጋጋጥና የህግ የበላይነትን ለማስከበር የተጀመረው ዘመቻ ዕውን እንዲሆን በሁሉም መስክ የሚያደርገውን ድጋፍ ያጠናክራል ብለዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን በምርምርና ጥናት የድሬዳዋና አካባቢውን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሃብቶች ለሀገር ልማትና ዕድገት፣ ለዜጎች የሥራና የማህበራዊ ችግሮች ማቃለያ እንዲሆኑ ዘንድሮ ከመቼውም ጊዜ በላይ በርካታ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በ1999 ዓ.ም. የመማር ማስተማር ሥራ የጀመረ ሲሆን፤ ከ18 ሺ በላይ ተማሪዎችን በመጀመሪያና በሁተኛ ድግሪ መርሃ-ግብሮች እያስተማረ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም