የጉጂ ዞን ወጣቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመደገፍ ወደ ግንባር ሊዘምቱ ነው

74

ነገሌ፤ህዳር14/2014(ኢዜአ) የጉጂ ዞን ወጣቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጥሪን በመቀበል ሀገር የማዳን ትግል ለመሳተፍ መነሳታቸውን አስታወቁ፡፡

ከዞን ከወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች  የተውጣጡ ወጣቶች በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ዛሬ በነገሌ ከተማ መክረዋል፡፡

የጎሮ ዶላ ወረዳ ነዋሪ ወጣት አብዲ ኡስማን በወቅቱ እንዳለው፤ በመሪ ደረጃ ወደ ግንባር ዘምቶ የህይወት መስዋእትነት ለመክፈል እራስን ማዘጋጀት ከሀገር ጥልቅ ፍቅር የሚመነጭ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመደገፍ በራስ ፍላጎትና ተነሳሽነት በግንባር ዘምቶ የሀገሩን ሉአላዊነት ለማስከበር እየተካሄደ ባለው ትግል ለመሳተፍ መነሳሳቱን ነው የገለጸው።

 ወደ ግንባር የዘመቱት ዶክተር አብይ የጀግና ህዝብና የሀገር ፍቅር ተምሳሌት ናቸው ያለው ደግሞ የአዶላ ዋዩ ከተማ ነዋሪና የመድረኩ ተሳታፊ ወጣት ደበላ ሚኤሳ ነው።

እኔና ጓደኞቼ በግንባር ተሰልፈን ለሀገር ሉአላዊነት መከበር አባቶቻችን በአድዋ የሰሩትን የጀግንነት አኩሪ ታሪክ ለመድገም ተዘጋጀተናልም ብሏል፡፡

የአዶላ ሬዴ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ንጉሴ ገመዳ በበኩሉ፤ ሀገር ሲደፈር እንዳላየ የማይበት ትእግስትም ሞራልም የለኝም ነው ያለው፡፡

የዶክተር አብይ ወደ ግንባር መዝመት የሲያድባሬን  ጦር በካራ ማራ እና ኢጣሊያ ወራሪን ደግሞ  በአድዋ ድል ካደረጉ ባለታሪክ ጀግኖች መሪዎቻችን ተርታ ያሰልፋቸዋል ብሏል፡፡

የጉጂ ዞን ወጣቶች ሊግ ሃላፊ ወጣት ታሪኩ ጎበና በበኩሉ፤ እኛ  ወጣቶች በግንባር ተሰልፈን ሀገር የማዳን ታሪካዊ ሀላፊነትም ግዴታም ወድቆብናል ሲል ገልጿል፡፡

አሸባሪዎችንና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶችን ለመመከት ወጣቶች መከላከያ ሰራዊቱን የምንቀላቀልበት ጊዜው አሁን ነውም ብሏል፡፡

የህይወት መስዋትነት በመክፈል ሀገር ለማዳን በግንባር ቀደም የሚዘምት የሀገር መሪ እንዳለን ጠላትም ወዳጅም ሊገነዘብ ይገባል ብላው ወጣት ታሪኩ፡፡

የሀገራችንን መሪ ተከትለን የተከፈተብንን ጦርነት  ለመቀልበስ የምንሳሰለት ህይወት ያለም ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም