የምዕራባዊያንን ጣልቃ ገብነት ለመቃወም በኤምባሲዎች በር ላይ በቀን ፋኖስ የማብራት ትዕይንተ ህዝብ ሊካሄድ ነው

83

አዲስ አበባ ህዳር 14/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን እውነት እያዩ እንዳላዩ የሚመስሉ ምዕራባዊያንን ለመቃወም በቀን ፋኖስ የማብራት ትዕይንተ ህዝብ የፊታችን ሀሙስ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ "የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ጥምረት ለኢትዮጵያ ህዝብ" አስታወቀ።
የጥምረቱ ፕሬዚዳንት ጋሻው ሽባባው በመጪው ሀሙስ ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚቃወሙ የተለያዩ ትዐይንተ ህዝቦች ይከናወናሉ ብለዋል።

ትዕይንተ ህዝቡ መነሻውን አራት ኪሎ አድርጎ ወደ አሜሪካና እንግሊዝ ኤምባሲዎች  በመሄድ በኤምባሲዎቹ ፊትለፊት በቀን ፋኖስ በማብራት አካሄዳቸው ትክክል አለመሆኑ የሚገለጽበት ነው ተብሏል፡፡

በቀን ፋኖስ ማብራት  የተፈለገውም አንዳንድ ምዕራባዊያን የኢትዮጵያን እውነት እያዩ እንዳለዩ የሚያልፉበት አካሄድ ተገቢ አለመሆኑን ለመግለዕ እንደሆነ ተጠቁሟል።

በትእይንተ ህዝቡ የሃይማኖት አባቶች ጭምር እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን አንዳንድ ምዕራባዊያን የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስትን እውነትና ፍላጎት ያላዩና ያላወቁ በመምሰል በተቃራኒው የሚሄዱትን አካሄድ የሚቃወሙ ልዩ ልዩ መልእክቶች ይተላለፋሉ።

በእለቱ በመላው ሀገሪቱ  የሚገኙ አሽከርካሪዎች ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ ለ10 ደቂቃ ያህል መብራት በማብራትና ክላክስ ነማድረግ ተቃውሞውን ይደግፋሉ ተብሏል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የነጻነት ምሳሌ መሆኗን የጠቀሱት የጥምረቱ ፕሬዚዳንት ከሀገራት ጋር ባላት ግንኙነትና ጉርብትና  ስሟ ፍትሀዊ ባልሆነ መልኩ የማይነሳና ረጅም ታሪክ ያለት ሀገር ናትም ብሏል።

ኢትዮጵያ ከብዙዎቹ  የአውሮፓ ሀገራት ጋርም  ከ100 ዓመት በላይ የዘለቀ የእርስ በእርስ መልካም ግንኙነት ያላት መሆኑን ተናግረዋል።

ነገር ግን አንዳንድ ምዕራባዊያን አሁን ላይ ረጅም ዘመን ያስቆጠረውን መልካም  ግንኙነት ወደ ጎን በመተው በመገኛ ብዙሃኖቻቸው የሚያሰራጩት የሀሰት ፕሮፓጋዳ ተገቢነት የለውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም