ለተዋጊው ተጨማሪ አቅም የፈጠረው የመሪው ውሳኔ

55

ሰመራ ኅዳር 14/2014 (ኢዜአ) በካሳጊታ ግንባር አሸባሪውን ህወሃት የተዋጉት የ50 ዓመቱ የሃይማኖት መሪ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መዝመት ''የበለጠ መነሳሳት'' ፈጥሮብልኛል ይላሉ።
 የሠመራ ከተማ ነዋሪው ሼኽ መሐመድ ኖራ አሸባሪውን ህወሃት ለመፋለም ከቤታቸው ከወጡ ሰነባብተዋል።

ሼኽ መሐመድ በዚያ ግንባር ሰሞኑን የጠላት ምሽግን በመስበር በተመዘገበው ድል የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል።

ታዲያ የኢዜአ ሪፖርተር አግኝቷቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩን መዝመት ጉዳይ ሲያነሳላቸው''የዜግነት ግዴታዬን ለመወጣት የበለጠ መነሳሳትን ይፈጥርብልኛል'' አሉት።

አሸባሪውና ወራሪው ህወሀት በአገር ላይ የፈጸመውን ክህደት ለመመከት ወደ ግንባር ዘምተው፣ወራሪው የተመካበትን ምሽግ ከጓዶቻቸው ጋር አፍርሰው ዛሬም ለሌላ ግዳጅ በአዲስ መንፈስ መሪያቸውን እንደሚከተሉ ነው የገለጹት።

"የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ኢትዮጵያውያን የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ መነሳሳትን ይፈጥርላቸዋል" ሲሉም ሼኽ መሐመድ አክለዋል።

ወይዘሮ ሞሚና አብዱም " ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወሰዱት አቋም የተጣለባቸውን ህዝባዊ ሃላፊነት ለመወጣትና አገርን ከአፍራሽ ኃይሎች ለመታደግ ያላቸውን ቁርጠኝነት አይቼበታለሁ" ብለዋል።

እሳቸውም ከመሪያቸው ጎን በመቆም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

''አገርን መታደግ የሁሉም ኢትዮጵያውያን እንጂ፤ የመከላከያ ሠራዊት፣ የልዩ ሃይሎች ወይም የከፍተኛ አመራሮች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ነው '' ሲሉም ተናግረዋል።
ወጣት ሃንፍሬ ዓሊ ሚራህ በበኩሉ "የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ውሳኔ አመራሩ በተሰጠው መንግሥታዊ ሃላፊነት ሰላምና ደህንነት ከማስከበር በላይ፤ ለአገር አንድነትና ሉዓላዊነት በቁርጠኝነት እንዲነሳ ያደርገዋል" ብሏል።

እሱም የጠቅላይ ሚኒስትሩን አርአያነት ተከትሎ ለመዝመት መነሳሳቱን ገልጿል።

አቶ መሐመድ አወል በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ራሳቸውን ከፊት አስቀድመው ኢትዮጵያን ለመታደግ መወሰናቸው ተምሳሌትነቱ ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ።

"ውሳኔው የተደቀነብንን የህልውና አደጋ መቀልበስ ለጥቂቶች የሚተው ጉዳይ ያለመሆኑን ከማመልከቱም በላይ ዜጎችን አገርን የማዳን ዘመቻውን ለመቀላቀል ያነሳሳቸዋል" ብለዋል።

የአፋር ሕዝብ እንደ ሼክ መሐመድ የተከፈተበትን ወረራ በመመከት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን በማስከበር  ታሪክ ሰርቷል፤ መሪው ከፊት ቀድሞ ጦርነቱን ሲመራ ደግሞ መች ተዋጋንና ትግሉም፣ ድሉም በኢትዮጵያ አሸናፊነት እስኪጠናቀቅ ይቀጥላል ይላል።





 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም