“አሸንዳ/ሻደይ/አሸንድዬ የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝቦች የአንድነትና ወንድማማችነት ህያው ማስረጃ ነው” ---ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

299
አዲስ አበባ ነሓሴ15/2010 አሸንዳ/ሻደይ/አሸንድዬ የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝቦች የአንድነትና ወንድማማችነት ህያው ማስረጃ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። አሸንዳ/ሻደይ/አሸንድዬ በዓል የአንድ ክልል ወይም የኢትዮጵያ ሃብት ብቻ ሳይሆን የዓለም ጭምር መሆኑን በመገንዘብ በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በጋራ መስራት ይጠበቅብናልም ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሰሜን ኢትዮጵያ ከነሐሴ 16 ቀን ጀምሮ የሚከበረውን አሸንዳ/ሻደይ/አሸንድዬ በዓል በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል። በዓሉ የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝቦችን በባህል በዘር በቋንቋና በሃይማኖት ሳይለያዩ በአንድ ላይ ያስተሳሰረ የህዝቦች የተዘወተረ የአንድነት ገመድ መሆኑንም ገልጸዋል። በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ የአማራ፣ የአገው፣ የኩናማ፣ የትግራይ እና ኢሮብ ህዝቦች በአመጋገብ፣ በባህል፣ በአኗኗር ዘይቤያቸው መመሳሰልና መተሳሰርን የሚያሳየው ነው። አሸንዳ/ሻደይ ከኢትዮጵያ ውጭ በደቡብ ኤርትራ ጭምር የሚከበር በዓል መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የህዝቦችን አንድነትና ነፃነት ማሳያ ሃብት በመሆኑ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያለው ሚና የጎላ እንደሆነም ገልጸዋል። በመሆኑም በዓሉ የሰሜን ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአገራችን፣ የቀጠናችን ብሎም የዓለም ውብ ሃብት መሆኑን በመገንዘብ በዩኔስኮ በማይዳሰሱ መስህቦች እንዲመዘገብ በትጋት መስራት ይኖርብናል ብለዋል። በዓሉ የፍቅር የአንድነትና የሰላም በዓል እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙሉ መግለጫው ከዚህ በታች ቀርቧል በሁሉም አቅጣጫ ያሉትን የሃገራችን ህዝቦች እንዳይበታተኑ ያስተሳሰሩ፤ እንዳይለያዩ ያጣመሩ፤ እንዳይፈርሱ ያማገሩ በርካታና ጠንካራ ማጎች በሃገራችን ሁሉም ጫፎች በክብርና በፍቅር እዚህም እዚያም አሉ። ህዝቦቻችን በጋብቻ ተዛምደው በማንነት ተዋህደው የኖሩ፤ ያሉና የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው። ልክ እንደ ምስራቁ ደቡቡና ምዕራቡ ህዝባችን ሁሉ የሰሜን የሃገራችን ህዝቦችም በባህል፣ በቋንቋ፣ በዘር፣ በሃይማኖት ወዘተ ተሰናስለው፣ ተዋደውና፣ ተዋህደው የኖሩ ያሉ የሚኖሩ ስለመሆናቸው በርካታ የታሪክ፣ የባህል፣ የእምነትና የቋንቋ ማስረጃ ማቅረብ የሚያስፈልግ ሁኔታ ሳይሆን ህይወታቸው ውስጥ ከተረበረቡ እልፍ መገለጫዎቻቸው የሚስተዋል ግሩም እውነት ነው። የዚህ አንድነትና የጋራ ማንነት፣ የዚህ ዘመንን እንኳ የሚያስገብር ከነፍስ የተሸመነ እውነት ማሳያ ከሆኑ የማህበረሰባችን እሴት ባህሎች ውስጥ ደግሞ በአማራና በትግራይ ክልሎች የሚኖሩ የአማራ፣ የአገው፣ የኩናማ፣ የትግራይ እና ኢሮብ ህዝቦች መመሳሰልና መተሳሰርን የሚያሳየው የአሸንዳ/ሻደይ ክብረ በዓል አንዱና ምናልባትም ዋነኛው ነው። የዚህን በዓል አከባበር ለሚመለከት የውጭ ታዛቢ የሰሜን ህዝቦቻችን በሁሉም መለኪያ አንድ ህዝብ እንጂ ሁለት ወይም ሶስት ሆነው ሊታዩ እንደማይችሉ እሙን ነው። የሰሜኑ ክፍል የሃገራችን ህዝቦች ልክ እንደ ደቡብ ምስራቅና ምዕራቦቹ ህዝቦቻችን ከሚለያዩዋቸው ይልቅ አንድ የሚያደርጓቸው እንደሚበዙ ብዙ ከማስረዳት ይልቅ የአሸንዳን አንድ ሰበዝ በፍቅር ማሳየት ሁሉን ነገር ይገልጸዋል። ስለ አንድነታቸው ከመግለጽ ይልቅ ስለ ልዩነታቸው ለመግለጽ ይቸግራል። ምክንያቱም አንድ የሚያደርጓቸው መገለጫዎች ከሚለያያቸው ይበዛሉና ነው። አንዱን ከአንዱ ለይቶ ለመረዳት ማንነቱንና ብሄሩን በመጠየቅ ከአንደበቱ መስማት ካልሆነ በስተቀር ከአመጋገቡ፣ ከአለባበሱ፣ ከባህሉ፣ ከእሴቱና አኗኗሩ እንዲሁም ከክብረ በዓላቱ ተነስቶ ማንም ይህ ከዚህ ነው ያ ከዚያ ነው ለማለት አይችልም። የህዝቦቻችን ትስስር፣በማንም ጫና ወይም አስገዳጅነት ሳይሆን ከህዝቦቹ የጋራ ማንነትና የጋራ ታሪክ የሚቀዳና የትላንት ታሪካቸውም ሆነ የዛሬ እውነታቸው ነው። የነዚህን ህዝቦች የአብሮነት ታሪክና ባህል ስንመረምር የምናገኘው የአሸንዳ/ሻደይ በዓላቸው በየትኛውም የዘመን ሀዲድ ላይ የትኛውም መንገራገጭና ንትርክ ቢኖር እንኳን በሁል ጊዜም ህይወታቸው ሆነ በታሪክ መሰውያቸው ላይ ያለው እውነት አንድ እንደሆኑ የሚናገር፣ በሚመጣውም ዘመን አንድ ሆነው እንደሚቀጥሉ የሚያመለክት በርካታ ህያው ምስክር ያለበት ውብ ሰነድ ነው። የአሸንዳ-ሻደይ በዓልን የመሳሰሉት የጋራ እሴቶቻችን ከቀደምት አባቶቻችን ጋር በመንፈስ የሚያስተሳስሩን ድሮች፣ ወደፊትም አብረን እንድንጓዝ የሚያደርጉን መንገድና አጓጓዦቻችንም ጭምር ናቸው። ስለትናንት፣ ስለ ዛሬና ስለ ነገ አንድነትና አብሮነት ከሚናገሩ ህያው ምስክሮች አንዱ የጾመ ፍልሰታ ለማርያምን መፈታት ተከትሎ ከነሐሴ 16 ጀምሮ ቀጥሎ ባሉ ቀናት በተለያየ የእድሜ ደረጃ ያሉ ሴቶች በዋናነት ግን በወጣቶችና ልጃገረዶች የሚከበረው የአሸንዳ/ሻደይ በዓል ነው። ይህ በዓል በአገራችን ከሚከበሩ ደማቅና ሀሴት ከሚሞሉ በዓላት አንዱ ሲሆን፤ ከሌሎች በዓላት የሚለየውም የበዓሉ ባለቤቶች ሴቶች ወይም ወጣት ሴቶች መሆናቸው ነው። ይህ በዓል የሴት ልጆች በተለይም ወጣት ሴቶች አንገታቸውን አቀርቅረው በሚሄዱበትና በአደባባይ ወጥተው ፍላጎታቸውን በማይገልጹበት ወቅት ሁሉ በሙሉ ነጻነት ይልቁንም በጋራና በአደባባይ የወደዱትን የሚያሞግሱበት፣የጠሉትን ሃሳብና ተግባር በነጻነት የሚያወግዙበት ድንቅ በዓል ነው። የአሸንዳ/ሻደይ በዓል ዜጎቻችን ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹ ከፈቀድንና ባህል ካደረግነው የሚያስፈራንና የሚያስደነግጠን ሳይሆን በአሸንዳ/ሻደይ በዓል ላይ እንደሆነውና እየሆነ እንዳለው እጅግ ማራኪና ውብ የሆነ የጥንካሬና የነጻነት መገለጫ ሆኖ መኖር በፍቅር የምናከብረው ብቻ ሳይሆን የአብሮነታችን ማስረገጫ ማህተም ሆኖ ከየልባችን የምንኖረው ባህላዊ የአብሮነት ሙዳያችን ነው። ልክ በአሁኑ ሰዓት በአሸንዳ/ሻደይ እንደምንደሰተው ሁሉ ልጆቻችንና ቀጣዩ ትውልድ ሀሳብን በነጻነት በአደባባይ የመግለጽ ባህል ስላወረስናቸው ሲያሞግሱን ይኖራሉ። አሸንዳ /ሻደይ የሴቶች ውበት፣ክብር እና ነጻነት ማሳያ ብቻ ሳይሆን ነጻነት ረሷ ነጻ የምትወጣበትና በአደባባይም ስጋ ለብሳ የምትታይበት ታላቅ ቀን ነው። አሸንዳ/ሻደይ ስለ ሴቶች ክብር፣ ስለ ባህሎቻችን ውበት፣ ስለ ህዝቦቻችን ወንድማማችነትና አንድነት የሚናገር ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም መስክ ህዝቦቻችን ነጻ ቢሆኑ፣ ሃሳቦቻቸውን በነጻነት ነገር ግን በሰላም በአደባባይ የሚገልጹበት ሁኔታ ቢፈጠር ምንኛ ውብና ድንቅ ሃገር ሊኖረን እንደሚችል አፍ አውጥቶ የሚነገር ህያው ትዕምርት ከመሆኑም ባሻገር ለዘመናዊ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታችንም ከባህላዊው ድንቅ ሃብታችን ብዙ የምንመነዝርበት ሃብታችን ነው። አሸንዳ/ሻደይ ከሃገራችን አልፎ ለዓለም ቅርስነት የሚበቃ የማይዳሰስ ሃብት ነው።ይህ ሃብት ከሰሜናዊ ኢትዮጵያ አልፎ በደቡብ ኤርትራም ጭምር የሚከበር ውብ በዓል ሲሆን ልናከብረው፣ ልንከባከበውና ታሪካዊ እሴቱን ሳይለቅ ከትውልድ ወደ ትውልድ ልናስተላልፈው የሚገባን መሆኑ አጽንኦት ሰጥቼ ለመግለጽ እፈልጋለሁ። በአሉ የህዝቦቻችንን ትስስር አጉልቶ የሚያሳይ የጋራ ጸጋና ህዝባዊ በረከት እንጅ የምንጣላበት እንደ አላቂ ሃብት በድርሻ-ድርሻ የምንከፋፈለው አይደለም። ይህ አስደሳችና አስደናቂ ባህል የሰሜን አገራችንን ህዝቦች ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያ ህዝቦች፣ የኢትዮጵያውያንንም ብቻ ሳይሆን የዓለም ሃብትና ቅርስ መሆን እንዲችል በዓለም የማይዳሰስ ሀብትነት እንዲመዘገብ አጥብቀን መስራት ይኖርብናል። በዓሉን የምናከብረውና የምንንከባከበው የውጭ አገር ቱሪስቶችን ለመሳብ ወይም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት ሳይሆን ራሳችንን፣ ክብራችንን ታሪካዊ እሴቶቻችንና በልዩነታችን ውስጥ ያለውን የማይናወጥ አንድነት ለማሳየት ነው። ነገር ግን ይህንን ማድረግ የሚቻለው እና እሴቶቻችንን ከራሳችን አሳልፈን የዓለም ማድረግ የምንችለው በዋናነት ሰላም፣ አንድነትና ፍቅር ሲኖርና ተደምረን ጠንካራ ህዝቦች ስንሆን ብቻ ነው። ስለሆነም ልክ እንደ ባህላዊ እሴቶቻችንና በዓላቶቻችን ሰላማችንን፣ አገራዊ አንድነታችንን፣ አብሮነታችንን ልንከባከብ ልናጎለብት እና ልንጠብቅ ይገባል። ለሁላችንም መልካም የአሸንዳ/ሻደይ በዓል እንዲሆንልን ከልብ እመኛለሁ        ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘለአለም ትኑር          ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም