በትግራይ በወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ላይ ለውጥ ለማምጣት ይሰራል....ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

59
መቀሌ ግንቦት 9/2010 የትግራይ ወጣቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የሚያሳድግ ለውጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማምጣት እንደሚሰራ የክልሉ ምክትል ርዕስ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል አስታወቁ። በመቀሌ ከተማ ለሦስት ቀናት የተካሄደው የወጣቶች የሰላምና የልማት ኮንፍረንስ ተጠናቋል። "መንግስት ለወጣቶች የገባው ቃል በተስፋ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ያረጋግጣል" ያሉት ምክትል ርዕስ መስተዳድሩ፣ የወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማጎልበት በጥናት የተደገፈና ከልማት ሥራዎች ጋር የተሳሰረ ፕሮጀክት ተግባራዊ እንደሚደረግ አመልክተዋል። ወጣቶች በኮንፈረንሱ ያነሱዋቸው የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህ፣ የሙስናና  ሌሎች ጥያቄዎችን በመፈተሽ መንግስት ተገቢ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስድም አብራርተዋል። በአሁኑ ወቅት የተጀመረው የአመራር ሽግሽግ እንደሚጠናከር የገለጹት ዶክተር ደብረጽዮን፣ "ወጣቶች በሂደቱ ላይ ጉድለት አይተው ጥቆማ ካደረጉ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት ዝግጁ ነው" ብለዋል፡፡ ወጣቶች ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን በማገልበት በሰላምና መረጋጋት ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ አደረጃጀታቸውን የማጠናከር ሥራም እንደሚከናወን ነው የገለጹት። ዶክተር ደብረጽዮን አንዳሉት፣ ወጣቱ የሥራ ባህሉን የሚያጎለብትበትና አስተሳሰቡን የሚያነጹበት "አግበ የወጣቶች ማሰልጠኛ ማዕከል" በቆላ ተምቤን ወረዳ በቅርቡ ተከፍቶ ሥራ ይጀምራል። ማዕከሉ ወጣቶች ተደራጅተው በሀገራቸው የልማትና የዴሞክራሲ እንቅስቃሴ የሚመካከሩበት እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡ "ወጣቶች ከጫት፣ አደንዛዥ እጽና ሱስ ነጻና ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ በእነሱ ላይ የአስተሳሰብ ግንባታ ለማካሄድ ቅድሚያ ተሰጥቶ ይሰራልም " ብለዋል፡፡ በኮንፈረነሱ ላይ ከክልሉ ሁሉም ዞኖች፣ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እንዲሁም ከአዲስ አበባና ድሬዳዋ ተወክለው የመጡ የክልሉ ተወላጅ ወጣቶች ተሰታፊ መሆናቸው ታውቋል። ወጣቶቹ በተለያዩ ጉዳዮች ተወያይተው መግባባት ላይ በደረሱባቸው ሀሳቦች ላይ ባለ 11 ነጥብ የጋራ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል። በዚህም የአስተሳሰብ ልዩነትን በማክበር ከሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ወጣቶች ጋር አንድነታቸውንና አብሮነታቸውን ለማጎልበት እንደሚሰሩ በአቋም መግለጫቸው ላይ አረጋግጠዋል፡፡ ከድሬዳዋ በመምጣት በኮንፈረንሱ የተሳተፈችው ወጣት መስከረም ተክለሃይማኖት እንዳለችው ለሦስት ቀናት በተካሄደው መድረክ በሀገሪቱ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች በአግባቡ ለመገንዘብ አስችሏታል፡፡ "ወጣቶች በጊዚያዊ ችግር ሳንበረከክ የሚያጋጥሙን ተግዳሮቶች በጽናት መታገልና እንዴት መፍታት እንዳለብን ልምድና ትምህርት ያገኘሁበት መድረክ ነው" ስትልም አስረድታለች። "መድረኩ በመንግስት፣ በኢህአዴግና በወጣቶች ላይ ያሉ ክፍተቶችን እንድናይ አድርጎናል" ያለው ደግሞ ከቆላ ተምቤን ወረዳ ዓብዪ አዲ ከተማ የተወከለው ወጣት ተስፋይ ገብረመድህን ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም