ህብረተሰቡ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን በመውሰድ ራሱንና ቤተሰቡን እንዲጠብቅ ጥሪ ቀረበ

61

አሶሳ፤ ህዳር 13 / 2014(ኢዜአ) ህብረተሰቡ በነጻ የሚሰጠውን የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት በመውሰድ ራሱንና ቤተሰቡን ከበሽታው እንዲጠብቅ ጥሪ ቀረበ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለአሥር ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል፡፡

100 ሺህ ሰዎችን ለመከተብ ታቅዶ  በተጀመረው ዘመቻ  ክትባቱን ከወሰዱት የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሀላፊ አቶ ለሜሳ ዋውያ እንዳሉት፤ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ነው፡፡

ሆኖም  ህብረተሰቡ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል መጠቀምን ጨምሮ በበሽታው ላለመያዝ የሚያደርገው ጥንቃቄ እየቀነሰ መጥቷል ነው ያሉት።

ክትባቱን መውሰድ በኮሮናቫይረስ የመያዝና የመሞት እድልን ስለሚቀንስ ህብረተሰቡ ስለክትባቱ የሚሰራጨውን የተሳሳተ መረጃ መስማት እንደሌለበት አመልክተዋል።

ሰዎች ሳይዘናጉ ክትባቱን ፈጥነው በመውሰድ ለብዙዎች ሞት ምክንያት ከሆነው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተወካይ ወይዘሮ መስተዋት ሃይሉ በበኩላቸው፤ በኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት ላይ የሚነገረው ወሬ ተገቢነት እንደሌለው ተናግረዋል።

"የምናውቃቸው ሰዎችና ጎረቤቶቻችን ሲታመሙ እና ሲሞቱ እያየን በቸልታ ከማለፍ ይልቅ ፈጥነን በመከተብ ራሳችንን ከወረርሽኙ እንጠብቅ" ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ የክትባቱን ጥቅም ተገንዝቦ ለዘመቻው ውጤታማነት ተባባሪ እንዲሆን መልዕክት ያስተላለፉት ደግሞ የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን የግብር አሰባሰብ ዳይሬክተር አቶ ሰማኒ ሃሰን ናቸው።

ነዋሪዎች ክትባቱን ፈጥነው በመውሰድ ራሳቸውን ከኮሮናቫርስ ከመጠበቅ ባለፈ በክትባቱ ላይ የሚነገሩ የተሳሳቱ መረጃዎችን መመከት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ፈቃዱ ረጋሳ፤ ዛሬ በክልሉ በዘመቻ የተጀመረው የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት እስከ ህዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም. እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ለአሥር ቀን በሚቆየው ዘመቻ  100 ሺህ የክልሉ ነዋሪዎችን ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል።

የክልሉ ካቢኔ እና ርዕሰ መስተዳድር  ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አሸሪፍ ሃጂአኑር፤ የክልሉ  ከፍተኛ ሥራ አመራሮችና የሃይማኖት አባቶች በቀዳሚነት ከመከተብ ባለፈ በየተቋማቸው ህብረተሰቡን በማስተማር ለዘመቻው ስኬታማነት የበኩላቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡

በአሶሳ ከተማ ዛሬ በይፋ  በተጀመረው  ዘመቻ  የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የሥራ 

ሀላፊዎች ተከትበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም