ኢትዮጵያ ለሱዳንና ጅቡቲ ካቀረበችው የኤሌክትሪክ ኃይል 23 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ አግኝታለች

77

ህዳር 13/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ወራት ለሱዳንና ጅቡቲ ካቀረበችው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 23 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ።

የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለሱዳን 263 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ኃይል በሽያጭ አቅርባለች።

ከዚህም 13 ነጥብ 18 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል።

በተመሳሳይ ለጅቡቲ ከቀረበው 159 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ኃይል 9 ነጥብ 76 ሚሊዮን ዶላር፤በድምሩ 23 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት የምትልከው የኤሌክትሪክ ኃይል የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘት ባሻገር ከአገራቱ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክር እንደሆነም ነው የገለጹት።

አቶ ሞገስ አያይዘውም የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጨምሮ በግንባታ ላይ ያሉ ሌሎች ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ ለሌሎች አገራት የምታቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚጨምር ገልጸዋል።

በአገሪቱ የሚገኙ ግድቦች የሚያመነጩትን አቅም መጠቀምና ማሳደግ የሚያስችሉ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ዝርጋታ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ጎን ለጎንም የኃይል ማስተላለፊያ ጣቢያዎችን አቅም የማሳደግ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

እነዚህ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ወደፊት ሊኖር የሚችለውን የኃይል ፍላጎት ለማስተናገድ እንዲያስችሉ ሆነው በመገንባት ላይ መሆናቸውንም አክለዋል።

ኢትዮጵያ ወደ 4 ሺህ 500 ሜጋ ዋት ኃይል የምታመነጭ ሲሆን ይህንንም በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ወደ 17 ሺህ ሜጋ ዋት ለማድረስ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

የኤሌክትሪክ ኃይል ከምትሸጥላቸው ሱዳንና ጅቡቲ በተጨማሪም ለኬንያም መሸጥ የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው።

በቀጣይም ከሶማሌ ላንድ፣ከሶማሊያ፣ከታንዛኒያ፣ከኤርትራ፣ከደቡብ ሱዳን እና ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር ለመፍጠር የሁለትዮሽ ግንኙነት በማድረግ ላይ መሆኗን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

-አካባቢህን ጠብቅ

_ ወደ ግንባር ዝመት

_ መከላከያን ደግፍ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም