የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ድጋፋችንን አጠናክረን እቀጥላለን

63

ጎንደር፤ ህዳር 13/2014(ኢዜአ) የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለሀብቶች አስታወቁ።
በከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ የንግድ ስራዎች የተሰማሩ ባለሀብቶች ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚገመት ስንቅ በግንባር እየተፋለመ ለሚገኘው የጸጥታ ሃይሎች እንዲውል አስረክበዋል።

የባለሀብቶቹ ተወካይ አቶ ቢኒያም ጸጋዬ በርክክቡ ሥነ-ሥርዓት ወቅት እንዳሉት፤ሀገሪቱ ከአሸባሪው ቡድን ጥፋት ለመታደግ ኢትዮጵያውያን ለህይወታቸው ሳይሳሱ መስዋትነት እየከፈሉ ይገኛሉ።

እነዚህን ወገኖች  ከተረፈው ሳይሆን ካለው አካፍሎ መደገፍ የሁሉም ድርሻ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ባለሃብቶችም አቅማቸው የቻለውን በማዋጣት ለስንቅ የሚሆኑ ብስኩቶችንና ቴምሮቹን ማመቻቸታቸውን ገልጸዋል።

ስንቁ በደባርቅ ግንባር የአሸባሪውን ቡድን  በመፋለም ላይ ለሚገኙት ለመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች  እንዲውል ነው።

ድጋፉን ያደረጉት 12 ባለሀብቶች እንደሆኑና የህልውና ዘመቻው  በድል  እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን  አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል፡፡

ድጋፉን የተረከቡት የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ፤ ህዝቡ፣ ባለሀብቱና የመንግስት ሰራተኛው ለክተት ጥሪው ፈጥኖ ምላሽ በመስጠት አኩሪ ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአስተዳደሩ የተደራጁ ወጣቶችም አካባቢያቸውን ከሰርጎ ገቦችና ከጸጉረ ልውጦች ነቅተው በመጠበቅ በኩል ሰፊ ተሳትፎ እያደረጉ ናቸው ብለዋል፡፡

በከተማዋ አስተዳደር በክተት ጥሪው በጥሬ ገንዘብ 100 ሚሊዮን ብር፤ በስንቅ ዝግጅት ደግሞ 50 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ለማሰባሰብ የተጀመረው ርብርብ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም