አሸባሪው ቡድን የከፈተውን ጦርነት ምክንያት አድርገው የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት የሚፈልጉ አካላት አሉ

67

ህዳር 12/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሃት ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የከፈተውን ጦርነት ምክንያት አድርገው የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት የሚፈልጉ አካላት እንዳሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።

የፕሬስ ሃላፊዋ ተቀማጭነቱን ደቡብ አፍሪካ ካደረገው ‘’ኒውስሩም አፍሪካ’’ከተሰኘው ሚድያ ጋር ባደረጉት ቆይታ በወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በገለጻቸውም የኢትዮጵያ መንግስት አሸባሪው የህወሃት ቡድን ሀገር ለማፍረስ ለከፈተው ጦርነት ምላሽ በመስጠት ላይ ይገኛል ብለዋል።

በዚሁ ወቅት ይህንን ግጭት በመጠቀም የራሳቸውን ፍላጎት ከግብ ለማድረስ በመንግስት ላይ ጫና ለማሳደር የሚሰሩ በርካታ የውጭ ተዋናዮች እንዳሉ ቢለኔ ስዩም ተናግረዋል።

በርካታ የሳተላይት ምስል መረጃዎች እና ሌሎች ድጋፎችን ለአሸባሪው ቡድን የሚያቀብሉ አካላት እንዳሉ ከደህንነት ዘርፉ የሚደርሱ ተጨባጭ መረጃዎች ይጠቁማሉ ነው ያሉት።

በዚህ ደረጃ አሸባሪውን ቡድን መርዳት ኢትዮጵያን የሚጎዳ ነው ያሉት የፕሬስ ሃላፊዋ፤አፍሪካውያን እንደ አህጉር የራስን ሉዓላዊነት ለማስከበር የሚያደርጉትን ሁሉን አቀፍ ጥረት ማደናቀፍም እንደሆነ ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ ነጻነቷን እና ሉዓላዊነቷን በማስከበር ረገድ ያስመዘገበችው አኩሪ ታሪክ ለአፍሪካውያን ምሳሌ እንድትሆን አድርጓታል ያሉት ቢለኔ ስዩም፤’’ዛሬ ላይ ከኢትዮጵያ ጎን መቆም ለመጪው አፍሪካ ብሩህ ዘመን መቆም ነው’’ ብለዋል።

አንዳንድ የምዕራባውያን አገራት እና የሚድያ ተቋማት አሸባሪው ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች በዜጎችን ላይ የሚያደርሳቸውን አረመኔያዊ ግድያዎች፤ ማፈናቀል፤መድፈር፤ዝርፊያ እና ሌሎች የቡድኑን ጥፋቶችን ወደጎን በመተው መንግስት ማንነት ላይ የተመሰረተ እስራት እና እንግልት ፈጽሟል በሚል ጫና ያሳድራሉ ብለዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች እየፈጸማቸው ያሉ ጥፋቶችንም ባሳለፍናቸው ሳምንታት ውስጥ በሪፖርት መልክ ያወጡ ተቋማት እንዳሉም ጠቅሰዋል።

የሽብር ቡድኑ አዲስ አበባን ከቧል የሚለው መረጃ ሲኤንኤንን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባውያን ሚድያዎች ከሳምንት በፊት ያራገቡበት ሃላፊነት የጎደለው የሀሰት ዘገባ መሆኑን ገልጸው፤በዚህም ህዝብን ለማሸበር ሆንብለው የሰሩት የተቀናጀ የፕሮፓጋንዳ ስራ ነው ብለዋል።

በመሆኑም እውነታው እነዚህ አካላት እንደሚያራግቡት የሃሰት መረጃ ሳይሆን አዲስ አበባ እና ዙሪያዋ ሰላማዊ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ነው ያሉት።

የፕሬስ ሃላፊዋ አክለውም በአንዳንድ የምዕራባውያን አካላት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ስልጣን የያዘን መንግስት ከወራሪውና አሸባሪው ቡድን ጋር እኩል አድርጎ የማየት ዝንባሌዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል ።

ይህም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንዲሁም ህዝብ እና መንግስትን ባለማክበር የሚያደርጉት ጫና አካል ነው።

በመላው ኢትዮጵያ ደረጃ የታወጀው አስቸኳይ የጊዜ አዋጅ የሀገሪቱ የሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ በማለም ስራ ላይ የዋለ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም