መደ ወላቡ ዩኒቨርስቲ ሻሸመኔ ካምፓስ በጤናው ዘርፍ ያሰለጠናቸውን 167 ተማሪዎች አስመረቀ

187

ሻሸመኔ ኅዳር 12 /2014 (ኢዜአ) የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ሻሸመኔ ካምፓስ በጤናው ዘርፍ ያሰለጠናቸውን 167 ተማሪዎች ዛሬ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ አስመረቀ።

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ሻሸመኔ ካምፓስ  ፕሬዝዳንት ዶክተር ቢፍቱ  ገዳ በስነ ስርአቱ ላይ እንደተናገሩት   ካምፖሱ ዛሬ ተማሪዎችን ሲያስመርቅ ለ5ኛ ጊዜ ነው።

የጤና ሙያ ከሌሎች ሙያዎች  ለየት ባለ መልኩ ውድ የሆነውን የሰው ህይወት የማትረፍ ስራ ስለሆነ  ተማራቂዎች  ሰውን ከሰው ሳይለዩና ከሙስና በፀዳ መልኩ ሕብረሰስቡን ማገልገል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ደክተር  አህመድ ከሊል በበኩላቸው መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በዛሬው እለት በጤናው ዘርፍ  121 በመጀመሪያ ዲግሪ፣  46 ደግሞ  በሁለተኛ ድግሪ ማስመረቁን ተናግረዋል።

"ተመራቂ ተማሪዎች በተማራችሁት ሙያ ህዝቡን በታማኝነትና በታታሪነት እንድታገለግሉ "በማለት በአደራ ጠይቀዋል።

በአዋላጅ ነርስ የተመረቀችው  ኮኮቤ ቦጋሌ  "በተመረኩበት ሙያ ሰው መሆኑን ብቻ መሰረት አድርጌ ላገለግል ተዘጋጅቻለሁ" ብላለች።

በጤና መከንን በከፍተኛ ውጤት የተመረቀው መሐመድ ገመዳ በበኩሉ "በጤና ሙያ  መመረቅ  የሰውን ህይወት ለማትረፍ በመሆኑ ተግቼ እሰራለሁ" ሲል ቃል ገብቷል።

መደ ወላቡ ዩኒቨርሲት በ13 ዙር  ከ36 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያየ  ትምህርት መስክ ማስመረቁ ታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም