የሀገርን ሉዐላዊነት ማስከበር የሁላችንም ጉዳይ ነው

74

አርባ ምንጭ ህዳር 12/2014 /ኢዜአ/ የሀገርን ሉዐላዊነት ማስከበር ለመከላከያ ሠራዊት ብቻ የተሰጠ ሳይሆን የሁላችንም ጉዳይ ነው ሲሉ በአርባ ምንጭ የሃይሌ ሪዞርት ሠራተኞች ገለጹ፡፡

ሠራተኞቹ በዛሬው ዕለት “እኔም ሃይሌ ነኝ” በሚል መሪ ሃሳብ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የገንዘብ ድጋፍና ደም ልገሳ አድርገዋል፡፡

የድርጅቱ ሠራተኛ ወጣት አልጠገብ አስቻለው እንዳለችው አሸባሪው ህወሃት በሀገር መከላከያ ሠራዊትና በንጹሃን ዜጎች ላይ  የፈጸመው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በታሪክ የማይረሳ ግፍ ነው፡፡

"በእኔ ዘመን እንደዚህ አይነት ጥቁር ታሪክ መመዝገቡ አሳዝኖኛል" ብላለች፡፡

"እኛ የሰላም አየር መተንፈስ የቻልነው የህዝብ ልጆች የሆኑት የመከላከያ ሠራዊት አባላት እየተዋደቁልን በመሆኑ ነዉ" ያለችው ወጣት አልጠገብ "የዜግነት ድርሻችንን ለመወጣት  ካለን ትንሽ ገቢ ለሰራዊቱ ድጋፍ አድርገናል " ብላለች።

ወጣት አልጠገብ  አክላም የውጭ መገናኛ ብዙሀን በኢትዮጰያ ላይ የሚያሰራጩትን የሀሰት ዘገባ በማውገዝ  በርካታ የዉጭ ዜጎች በምዕራባዊያኑ በሬ ወለደ ዜናዎች ሳይሸበሩ  ወደ ድርጅታቸው በመምጣት እየተስተናገዱ መሆናቸውን አስታውቃለች፡፡

"በቅኝ ያልተገዛች ሀገር ዜጋዎች እንደመሆናችን መጠን የውስጥም ሆነ የውጭ ጫናዎች የሚያጠነክሩን እንጂ ወደኋላ የምያደርጉን አይደሉም" ብላለች ፡፡

"በአገር ጉዳይ ቀልድ የለም፤ ሀበሾች ነንና ለየትኛዉም እጅ ጠምዛዥ ሃይሎች አንንበረከክም" ያለው ደግሞ ወጣት ኤፍሬም ካንታና ነው፡፡

እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለመከላከያ ሠራዊቱ ከእኛ ምን ይጠበቃል ለሚለው በራስ ተነሳሽነት ምላሽ ለመስጠት ይህ ፕሮግራም መዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡

"ስንተባበር አቅም እንሆናለን ፤በተባበረ ክንዳችን የኢትዮጵያን ሰላም እናረጋግጣለን" ብሏል።

የድርጅቱ ሰራተኛ ወጣት ናርዶስ ገብረማሪያም በበኩሏ "አሸባሪዎች በዜጎች ላይ የፈጸሙት ግፍና በደል በጣም አሳፋሪና መንፈስን የሚረብሽ ነው" ብላለች፡፡

"ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ የምንችለው የመጣብንን ፈተና በጋራ ቆመን ስንመክት ብቻ ነው" ስትል ገልጻለች።

"ታሪክ መሥራት ልማዳችን ነው" ያለችው ወጣቷ "የሀገርን ሉዐላዊነት ማስከበር ለመከላከያ ሰራዊት ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁላችን ጉዳይ ነው" ስትል አመልክታለች ፡፡

በአርባ ምንጭ ሃይሌ ሪዞርት የሚገኙ 200 ሠራተኞች በዛሬው እለት ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከወር ገቢያቸው 100 ሺህ ብር  የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍና 50 ዩኒት ደም ለግሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም