የአዊ ዞን አርሶ አደሮች ማሳቸውን ከአረምና ተባይ ለመከላከል በትኩረት እየሰሩ ነው

121
ባህር ዳር ነሓሴ 15/2010 በዘንድሮው የኸር ወቅት ከሚያከናውኑት የእርሻና የዘር ስራ በተጓዳኝ የአረምና ተባይ መከላከልን ትኩረት ሰጥተው በመስራት ላይ መሆናቸውን በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮች ተናገሩ። አርሶአደሮች አረምን ለማስወገድና ተባይን ለመከላከል እያከናወኑ ያሉት ተግባር ለምርታማነት እድገት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል። በዞኑ አየሁ ጓጉሳ ወረዳ የሶስቱ ሰኞ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መለሰ ኃይሌ እንዳሉት ስድስት ሄክታር መሬታቸውን በበቆሎ፣ ዳጉሳና በርበሬ ሰብሎች ዘር ሸፍነው እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል። መርታማነትን ለማሳደግም በተለይ የበቆሎ ማሳቸውን እስከ ሶስት ጊዜ የአረም ስራ ያከናወኑ ሲሆን የዳጉሳና የበርበሬ ማሳቸውን ደግሞ የመጀመሪያ ዙር የአረም ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል። እንዲሁም በግማሽ ሄክታር የቆሎ ማሳቸው ላይ የተከሰተውን ተምች በእጅ በመልቀምና ኬሚካል በመርጨት መከላከል መቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡ ሶስት ሄክታር መሬታቸውን በተለያዩ ሰብሎች በማልማት የተባይና የአረም መከላከል ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በዚሁ ወረዳ የኢንባራ ቀበሌ ነዋሪ ሼህ ሰኢድ አህመድ ናቸው። በምክረ ሃሳቡ መሰረት ግብአትን በመጠቀማቸው ማሳውን ከአረምና ተባይ በመከላከላቸው ባለፈው ዓመት በአንድ ሄክታር ካለሙት የበቆሎ ማሳ 110 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡ በተያዘው ዓመትም ከዚህ የተሻለ ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ በአዊ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ አንዷለም አያሌው በበኩላቸው በዘንድሮው የመኽር ወቅት በዞኑ ከ270 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብል ዘር የመሸፈን ስራ እየተከናወነ ነው፡፡ እስካሁንም 237 ሺህ 743 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር ተሸፍኖ እየለማ ሲሆን ቀሪውን በጤፍ፣ ሽምብራና ሌሎች የጥራጥሬ ዘር የመሸፈን ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ምርታማነትን ለማሳደግም 63 ሺህ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም የተሸፈነ ሲሆን ከ320 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በዞኑ 10 ሺህ 710 ሄክታር  በለማው  መሬት ላይ የተከሰተውን ተምች በበህላዊና በኬሚካል ርጭት 98 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆነውን  መከላከል መቻሉን ገልፀዋል፡፡ ለመከላከል ስራው 2ሺህ 300 ሊትር ፀረ ተባይ ኬሚካል ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ከ31 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች ተምቹን በባህላዊ መንገድ በማስወገድ ስራ ተሳትፈዋል፡፡ አርሶ አደሩ የበቆሎ፣ ዳጉሳ፣ ጤፍና ሌሎች ሰብሎችን በደቦና አደረጃጀትን መሰረት አድርጎ የሚያካሂዱ የአረምና ተባይን የመከላከል ስራ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም