የአሜሪካ መንግስት በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን የኢትዮጵያ መንግሥት መደገፍ አለበት

82

ህዳር 12/2014 (ኢዜአ) የአሜሪካ መንግስት በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን የኢትዮጵያ መንግሥት መደገፍ አለበት ሲሉ በኢትዮጵያ ለጉብኝት የመጡት አሜሪካዊቷ ሜሊሳ ዳቢ ገለጹ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት አሜሪካዊቷ ሜሊሳ ዳቢ፤ የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ከመጣል መቆጠብ እንዳለበትም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በህዝብ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ በተካሄደ ምርጫ ወደ ሥልጠን የመጣው መንግሥት ላይ ማዕቀብ መጣል ተገቢም፣ ፍትሃዊም አይደለም ብለዋል።

አሜሪካዊያኖች ኢትዮጵያን ይወዳሉ ነገር ግን በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መረዳት የሚችሉበት ትክክለኛ መረጃ እያገኙ አለመሆኑንም ዳቢ ጠቅሰዋል።

ሲ ኤን ኤን፣ ቢ ቢ ሲ፣ አልጀዚራና ሌሎችም ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ኢትዮጵያን በተመለከተ የሐሰት መረጃ እያስተላለፉ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ሰግተው እንደነበር ገልጸው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ ሚዲያዎቹ ያሰራጩት መረጃ ትክክል አለመሆኑን መረዳታቸውን ተናግረዋል።

አሸባሪው የሕወሃት ቡድን በርካታ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት መፈጸሙን ጠቁመው ምዕራባውያኑ ከአሸባሪው ቡድን ጋር መቆማቸው ግርምት እንደጫረባቸው ገልጸዋል።

አሸባሪው ሕወሃት በንጹሃን ላይ ከፍተኛ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እየፈጸመ መሆኑን ጠቁመው አገሪቷ ሰላም እንዳይኖራት የሚሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት።

በመሆኑም ምዕራባውያኑ አሁን የያዙትን የተሳሳተ አቋም በመቀየር የኢትዮጵያን ሕጋዊ መንግሥት መደገፍና ሕወሃትም አሻበሪ ቡድን መሆኑን መቀበል አለባቸው ነው ያሉት።  

ኢትዮጵያና አሜሪካ የቆየና ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው አገራት መሆናቸው ይሄው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ሜሊሳ ዳቢ ተናግረዋል።   

ኢትዮጵያና አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1903 ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም