ህብረተሰቡ ባልተገባ ወሬ ሳይዘናጋ የኮቪድ- 19 ክትባትን ሊወስድ ይገባል

76

ጅማ፣ህዳር 12/2014 (ኢዜአ) ህብረተሰቡ ባልተገባ ወሬ ሳይዘናጋ የኮቪድ 19 ክትባትን በመውሰድ እራሱን ከበሽታው ሊጠብቅ እንደሚገባ የጅማ ዩኒቨርሲቲ አሳሰበ።

በጅማ ከተማ ከነገ ጀምሮ ለ34 ሺህ  የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም እንደ ጅማ ዞን በሚቀጥሉት 10 ቀናት ለ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች  የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት እንደሚሰጥ ተመላክቷል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የአደጋ ጊዜ ትግበራ ማእከል የቫይረሱን ስርጭትና የክትባቱ አሰጣጥ ተግዳሮትን በማስመልከት  ትላንት የውይይት የመድረክ አካሂዷል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ሀኪም ፕሮፌሰር ኢሳያስ ከበደ በወቅቱ አንዳሉት ከኮቪድ 19 ክትባት ጋር ተያይዞ የሚነገሩ ያልተገቡ ወሬዎች ህብረተሰቡን እያዘናጉ ነው።

ከክትባቱ ጋር በተያያዘ የሚናፈሱ ያልተረጋገጡ ወሬዎች ህብረተሰቡ ክትባቱን በጥርጣሬ አንዲመለከተው ያደረገው መሆኑን ጠቁመው  ህብረተሰቡ ባልተገቡ ወሬዎች ሳይዘናጋ ክትባቱን በመውሰድ እራሱንና ሌሎችን ከበሽታው ጥቃት እንዲጠብቅ አሳስበዋል ።

"በአንዳንድ ሀገራት ክትባቱን ከወሰዱ ከ1ሚሊዮን ሰዎች አንድ ሰው ላይ የደም መርጋትና ሌሎች የጎንዮሽ ችግሮች ማጋጠሙን ጠቅሰው "ይህ አሳሳቢ ሊሆን አይገባም" ሲሉ አስገንዝበዋል ።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ በበኩላቸው ቫይረሱ የዩኒቨርሲቲውን ባልደረቦች ጭምር በሞት የነጠቀ  መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለው የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ ክትባቱን በአግባቡ መከተብና የተለመዱ የቫይረሱን መከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም ችላ ማለት እንደማይገባ አስገንዝበዋል።

የጅማ ከተማ የጤና ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ኢንዲያ መሀመድ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ለ12 ሺህ ሰዎች ክትባቱ መሰጠቱን አስታውሰው፤ ነገ በሚጀመረው የክትባት ዘመቻም ለ34 ሺህ  የህብረተሰብ ክፍሎች ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።

በጅማ ዞን ደረጃም በሚቀጥሉት 10 ቀናት ለ1 ነጥብ 5  ሚሊዮን ሰዎች  ክትባቱ  እንደሚሰጥ  ያስታወቁት ደግሞ  የዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፎአድ ሳቢት ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም