የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ የገጠሙትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተጠቆመ

63
ሚዛን ነሀሴ 15/2010 የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ የገጠሙትን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ከፓርኩ የሚገኝ ገቢ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ፡፡ በኦሞ ብሔራዊ ፓርክ መሠረታዊ ችግሮችና ፓርኩን በዘላቂነት ማልማት ስለሚቻልበት ሁኔታ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት በሚዛን ከተማ ምክክር ተካሂዷል፡፡ በምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በኦሞ ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ የሚኖሩት አቶ ወርቁ ኢያርዝ  እንዳሉት በፓርኩ ውስጥ ከዚህ ቀደም ዝሆንን ጨምሮ የተለያዩ የዱር እንስሳት ይገኙ ነበር፡፡ ''ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  ግን ፓርኩ ተገቢውን ጥበቃ ባለማግኘቱ በውስጡ የነበሩ ብርቅዬ እንስሳት በመጥፋት ላይ ይገኛሉ'' ብለዋል፡፡ ፓርኩ ባለመከለሉና ስለፓርኩ ጥበቃና ደህንነት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በቅርበት ባለመሰራቱ ሰዎች በቀላሉ ወደ ፓርኩ በመግባት ህገወጥ አደንና የደን ጭፍጨፋ እንዲፈጽም  ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ የሚመለከተው አካልም ፓርኩን ከጥፋት ሊታደገው እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ በቤንች ማጂ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ባለሙያ አቶ ካሳሁን ከበደ በበኩላቸው ''ወደ ፓርኩ የሚያደርስ መንገድና ሌሎች የመሠረተ ልማት ተቋማት አለመሟላት ፖርኩ በተገቢው መንገድ እንዳይጎበኝ አድርጎታል'' ብለዋል፡፡ የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ በከፍተኛ ሁኔታ ብዝሀ ሕይወት ያለው በመሆኑ  የጉብኝት መዳረሻ ቢሆንም በፖርኩ አካባቢ ያለው መሠረታዊ ችግር በጎብኝዎች ተመራጭ እንዳይሆን ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ አቶ ኑር ይመር እንዳሉት ፓርኩ ያሉበትን መሠረታዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የፌዴራል መንግስትን ድጋፍ ይጠይቃል፡፡ የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ በጎብኝዎች የሚፈለጉ ገጽታዎች ያሉት ቢሆንም የመሠረተ ልማት ችግሩ ከሚፈለገው ባነሰ ሁኔታ እንዲጎበኝ አድርጎታል ነው ያሉት፡፡ ፓርኩን ሁለት ዞኖችና አምስት የአርብቶ አደር ወረዳዎች የሚያዋሰኑት ሲሆን በዙሪያው የሚገኙ ማህበረሰቦችን በማሳተፍ የፓርኩን ደህንነት ለመጠበቅ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡ በፌዴራል ዱር አንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አስቻለው ጸጋዬ በበኩላቸው የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የዳግም ወሰን ማካለል ስራ ቅድሚያ ተሰጥቶት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ በማካለል ሥራው ዙሪያም በቀጣዩ ሣምንት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም