የድሬዳዋ ነዋሪዎች የዋጋ ንረትን ለማርገብ የተጀመረው የሰንበት ገበያ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠየቁ

110

ድሬዳዋ፤ ህዳር 11/2014 (ኢዜአ) በድሬዳዋ ኅብረተሰቡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ በመጣውን የዋጋ ንረት ሳቢያ የሚስታወለውን የኑሮ ውድነትን እንዲቋቋም የተጀመረው የቅዳሜና የእሁድ ገበያ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ነዋሪዎች አሳሰቡ።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገበያው አመቺ በሆኑ አካባቢዎች እንደሚስፋፋ አስታውቋል፡፡


የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ካለፈው ወር አጋማሽ ጀምሮ ሸማቾችን፣ ነጋዴዎችንና አምራቾችን በቀጥታ የሚያገናኝ የቅዳሜና የእሁድ ግብይት በሥራ ላይ አውሏል፡፡

ገበያተኞቹ ለኢዜ አበሰጡት አስተያየት በገበያው በበቂ መጠንና በታላቅ ቅናሽ እየቀረቡ ያሉት የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

ይህም የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠርና በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶቹን ለማግኘት ያስችለናል ብለዋል።

ከገበያተኞቹ መካከል አቶ አምበስ እንግዳ እንዳሉት የታሸገ አምስት ሊትር ዘይት በሌሎች መደብሮች ከሚሸጥበት በ100 ብር፣ አንድ ካርቶን ብስኩት በ150 ብር ቅናሽ ገዝቼያለሁ፡፡

ወይዘሮ ኑሪያ ዓሊ በከተማዋ የቅዳሜና የእሁድ ገበያ መጀመሩ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የሸቀጦች ዋጋ ለማረጋጋትና የኑሮ ውድነት ለመቋቋም አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በገበያው በስኳር፣ በፓስታና በጓሮ አትክልት በኪሎ ከስምንት እስከ 15 ብር በቅናሽ መግዛታቸውን   ገልጸዋል፡፡

የቅዳሜና የእሁድ ገበያ ለኑሮ ውድነቱን መቀነስ መሠረታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ያሉት ደግሞ አቶ ዮሐንስ ጥበቡ ናቸው፡፡

አስተዳደሩ የሸቀጦቹን ዋጋ ለማስወደድ ከሸማቾች ጋር ተሻምተው የሚገዙ ቸርቻሪ ነጋዴዎችን መቆጣጠር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ነጋዴው አቶ ኢዮብ ሐሰን በገበያው የሚያቀርቧቸው የፋብሪካ ምርቶች በቀጥታ ለሸማቾች እየደረሱ በመሆናቸው ደስታ እንደሚሰማቸው ተናግረዋል፡፡

ገበያ በአራቱም ማዕዘናት ቢስፋፋ  ሸማቾች በስፋት  ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላልም ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር የኑሮ ውድነት ለመቀነስ የገበያ ዋጋን ከጥቅምት 2014 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በተካሄዱ ገበያዎች ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች ከ11 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚጠጋ ግብይት አከናውነዋል፡፡

ሸማቾቹ ያቀረቧቸው መሠረታዊ የገበያ ክፍተቶች በማሻሻልና የመገበያያ ሥፍራዎችን በማስፋት የኑሮ ውድነት የመቀነስና ገበያን የማረጋጋት ሥራ እንደሚጠናከር ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ችግር ለመሻገር የንግድ ማህበረሰቡ ነዋሪዎችን በታማኝነትና በቅንነት እንዲያገለግል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም