ማህበሩ ከ10 ሺህ ለሚበልጡ ሴቶችና አረጋውያን ድጋፍ አደረገ

91

ጎንደር ህዳር 11/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በደባርቅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ከ10 ሺህ በላይ ሴቶችና አረጋውያን ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

በማህበሩ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ሻምበል ዋለ ለኢዜአ እንደገለጹት ማህበሩ ለተፈናቃዮች  120 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ አድርጓል።

በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ለተፈናቀሉት ወገኖች ካደረገው ድጋፍ ውስጥ 80 ሚሊዮን ብር ለምግብ አገልግሎት እንዲውል የተለገሰ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም በነፍስ ወከፍ ለተፈናቃይ 8 ሺህ ብር በግል በከፈቱት የባንክ ሂሳብ ገቢ መደረጉን ኃላፊው አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም ግምታቸው 40 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ብርድ ልብሶች፣ የመመገቢያ፣ የማብሰያና የመጠጫ ቁሳቁስ  ማከፋፈሉን ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም ለሴቶች የግል ንጽህና መጠበቂያ የሚያገለግሉ ቁሳቁስን ጨምሮ የመኝታ ምንጣፎችና በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የቤት ውስጥ መብራቶች መለገሱን አቶ ሻምበል አስታውቀዋል፡፡

''በ80 ዓመቴ በወራሪው የሽብር ቡድን ከቤት ንብረቴ ተፈናቅዬ ጧሪ አልባ በመሆን ለተረጂነት ተዳርጌአለሁ'' ያሉት ደግሞ ከአዲአርቃይ ከተማ የተፈናቀሉት እማሆይ ብዙነሽ ተፈራ ናቸው፡፡

''መንግሥት የሽብር ቡድኑን ደምስሶ መቀበሪያዬን በትውልድ ስፍራዬ እንዲያደርግልኝ ፀሎቴና ምኞቴ ነው'' ብለዋል። ማህበሩ ባደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን በመግለጽ።

አካል ጉዳተኛዋ ወይዘሮ ታምሬ መሳፍንት በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት በአዲአርቃይ ከተማ ወጣቶችንና አቅመ ደካሞችን ጭምር ሲያሰቃይና ሲገድል በማየቴ እኔም ህይወቴን ለማትረፍ አራት ቀናት በእግር ተጉዤ ደባርቅ ከተማ በመግባት ህይወቴን ማትረፍ ችያለሁ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርና መንግሥት ላለፉት አራት ወራት ባደረጉላቸው ድጋፍ ችግራቸውን ለመቋቋም እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

በወራሪው የህወሓት የሽብር ቡድን ከአዲርቃይ ከተማ ሶስት ልጆቻቸውን ይዘው ቤት፣ ንብረታቸውንና ባለቤታቸውን ጥለው ወደ ደባርቅ ከተማ ለመሰደድ መገደዳቸውን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ሙሉ አለልኝ ናቸው፡፡

ባለቤታቸው በአሁኑ ወቅት ወራሪውን በግንባር በመፋላም ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ማህበሩ ለእሳቸውና ለልጆቻቸው ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በደባርቅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ከ30 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም