ኢንተርፕራይዙ በባሌ ዞኖች በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ

78

ጎባ ህዳር 11/2014 (ኢዜአ)--- የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ በሁለቱ የባሌ ዞኖች የዝናብ እጥረት ባስከተለው ድርቅ ለችግር ለተጋለጡ ዜጎችና እንስሳት ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የምግብ እህልና የመኖ ድጋፍ አደረገ፡፡

የኦሮሚያ አደጋ ስጋት ስራ አመራርና የልማት ተነሺ ኮሚሽን በበኩሉ በክልሉ የተለያዩ ዞኖች የዝናብ እጥረት ያስከተለው ድርቅ  በሰውና በእንስሳት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ  በጀት መድቦ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የከተሞች ክላስተር አስተባባሪና የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አዲሱ አረጋ የተመራው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ ድጋፉን ለሁለቱ የባሌ ዞኖች ዛሬ በባሌ ሮቤ አስረክቧል፡፡

አቶ አዲሱ አረጋ በርክክብ ሥነስርዓቱ ላይ እንዳሉት የክልሉ መንግስት በኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖች የዝናብ እጥረት ያስከተለው ድርቅ በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በጀት መድቦ በትኩረት እየሰራ ነው፡፡

በተለይ በስጋት ስራ አመራርና የልማት ተነሺ ኮሚሽን አማካይነት ለምግብ እህል ግዥ፣ ለውኃ አቅርቦትና ለሳር ግዥ አስፈላጊውን በጀት መድቦ ወደ የዞኖቹ  እያሰራጨ  መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 በዞኖቹ ቆላማ አካባዎች እየተገነቡ ያሉት የዌልመልና ያዶት የመስኖ ሜጋ ፕሮጄክቶችን ጨምሮ ሌሎችንም በማጠናቀቅ በተደጋጋሚ በሚከሰተው ድርቅ የሚያጋጥመውን የጉዳት ተጋላጭነት ለመቀነስ በትኩረት ይሰራልም ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ ለድርቅ ተጎጂዎቹ ያደረገው ድጋፍ የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን የገለጹት አቶ አዲሱ ሌሎች ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

የኦሮሚያ አደጋ ስጋት ስራ አመራርና የልማት ተነሺ ኮሚሺነር አቶ ሙስጠፋ ከድር በበኩላቸው በክልሉ በጉጂ፣ በቦረና፣ በምዕራብና ምስራቅ ሀረርጌ እንዲሁም በባሌ እና ምስራቅ ባሌ አካባቢዎች የክረምት ዝናብ ባለመጣሉ መጠኑ ቢለያይም ድርቅ መከሰቱንም ገልጸዋል።

መንግስት በድርቁ ምክንያት በሰውና በእንስሳት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ 100 ሚሊዮን ብር መድቦ እየሰራ ነው ብለዋል።

የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሽኔ ቦጋላ በበኩላቸው ኢንተርፕራይዙ በዋናነት በሀገሪቱ በአርሶ አደሩ ዘንድ የሚታየውን የምርጥ ዘር አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ኢንተርፕራይዙ የምርጥ ዘርን ተደራሽ ከማድረግ በተጓዳኝ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚታየውን የማህበራዊ አገልግሎት ችግሮችን ለማቃለል ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢንተርፕራይዙ ያደረገው ድጋፍ 2ሺህ  ኩንታል የምግብ እህልና 1ሺህ 600 ቤል የሳር እስር መሆኑን የጠቆሙት ዶክር አሽኔ የተደረገው ድጋ በገንዘብ ሲተመን ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡

የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ በበኩላቸው ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው የችግሩን ስፋት ከግምት ውስጥ በማስገባት ሌሎች ግለሰቦችና ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም